በህገ መንግሥቱ ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን ፀንቷል

ዘንድሮ ለ12ኛ ጊዜ የሚከበረው የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በያዝነው ወር ህዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰመራ ከተማ ይከበራል። ይህ ዕለት የአገራችን ህዝቦች አስከፊውን የደርግ ሥርዓት ከላያቸው ላይ አሽቀንጥረው በመጣል የቃል ኪዳናቸው ማሰሪያ የሆነውን ህገ መንግሥት ያፀደቁበት ነው። በሙሉ ፈቃዳቸው አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብን ለመገንባት በደማቸው የፃፉትን ሰነድ እውን ያደረጉበት ታላቅ እለትም ነው — ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም። የዛሬ 23 ዓመት። እናም ከዘንድሮው ክብረ በዓል በመነሳት ስለ ህገ መንግሥቱ ዋነኛ መሠረታዊ ነጥቦችን በማነሳሳት ጥቂት ማለት ተገቢነት ይኖረዋል።
የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት በባህሪው ተራማጅ እንደመሆኑ መጠን፤ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚፈጥር ነው። የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህገ መንግሥቱን የዛሬ 23 ዓመት ገደማ ሲያፀድቁ በጋራ ፍላጎት ላይ ተመስርተው በመሆኑ ገና ከጥንስሱ ጀምሮ ህገ መንግሥቱ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚያጎናፅፍ መሆኑ ግልፅ ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ ህገ መንግሥቱ የሁሉንም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነትን አጎልብቷል። ለዚህም በህዝቦች መካከል የነበረው የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሳቤ ከፍተኛውን ድርሻ መጫወቱ እርግጥ ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባሉበት አገር ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መኖሩ የግድ ነው። ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እስከተጠናከረ ድረስ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መኖሩ አያጠያይቅም። ባለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት የተከናወነው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን የማጎልበት ጥረት ምንም ችግር አልነበረበትም ማለት አይቻልም። ባለፉት ሥርዓቶች ከነበሩት ውስብስብ የብሔር ጭቆናዎች አንጻር አስተሳሰቡን በቀላሉ ማስረፅ አስቸጋሪ ነበር። ይሁንና ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የአገራችንን አንድነት በማጠንከር ኢትዮጵያዊነት እንዲያብብ እያደረገ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። በእርግጥም ብሔራዊ ማንነት ተደፍቆ ኢትዮጵያዊነት ሊመጣ አይችልም። ተከባብሮ እንጂ። ባለፉት 257 ዓመታትም ሁሉም ማኅበረሰብ በራሱ ቋንቋ የመናገር መብቱ የተጠበቀለት በዚሁ ፅንሰ ሀሳብ መነሻነት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።  
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም የተተገበረው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ዛሬ ላይ ፍሬ ማፍራት ችሏል፡፡ ምክንያቱም ፅንሰ ሃሳቡ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በሠላም አብሮ የመኖርና ችግርንም በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ማኅበረሰባዊ ግንኙነትን በብቸኝነት መከተል ነውና፡፡ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በመጎልበት ላይ ይገኛል። ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ከትምክህትና ከጠባብ ኃይሎች ጋር ለሚደረግ ትግል ዓይነተኛ መሣሪያ መሆኑ ይታወቃል። ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የራስን ማንነት እንደሚያከብር ሁሉ ሌሎችም በተመሳሳይ አሉ ብሎ የመቀበል ጉዳይ በመሆኑ መተሳሰብንና የጋራ ልማትን ያረጋግጣል።
ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ሁነኛ መሣሪያ ነው። በመሆኑም ጽንሰ ሃሳቡ የበላይነት ባገኘባቸው አካባቢዎች እና ክልሎች ምንም ዓይነት ግጭት ሊከሰት አይችልም። ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የጋራ የልማት ተጠቃሚነትን ስለሚያረጋግጥ ነው። በመሆኑም ይህንን ይበልጥ ለማስቀጠል አልፎ…አልፎ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚስተዋሉትን የጠባብነት እና የትምክህት አስተሳሰቦች በጋራ መዋጋት ያስፈልጋል።
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በብሔሮች መካከል የአመለካከት ዝምድና መፍጠር ችሏል፡፡ በመሆኑም አገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ያደረሰ እሴት ሆኗል።  የትምክትና ጠባብነት ፈተናዎች በአገራችን ቢኖሩም፣ በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መሸነፋቸው አይቀርም።  
በአንዳንድ አካባቢዎች "የትምክህት ሐሳባችንን በነፃነት እንግለጽ፣ አትንኩን" የማለት ነገር ይታያል፡፡ ይህንን አመለካከት መሸሸጊያ የሚያደርጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ ህገ መንግሥቱም አስተሳሰባቸውን በነፃነት እንዲገልጹ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ሆኖም ኢሕአዴግም ሆነ መንግሥት የተለየና የተሳሳተ ሐሳብ ያላቸው ሰዎች ቢሆኑም ሃሳባቸውን ለምን ይገልጻሉ የሚል ብዥታ ኖሯቸው አያውቅም፡፡
ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነትን ብሎም ህዝባዊ ወገንተኝነትን ለማረጋገጥ ወሣኝ ጉዳይ ነው፡፡ ለአንድ ህዝብ የሚቆረቆር፣ ለሌላውም ህዝብ መቆርቆር ይኖርበታል። ምክንያቱም አንዱ ሌላኛውን በእኩልነት ሲያከብር በአንፃሩ ደግሞ  መከበርን ያተርፋል፡፡ ያለፈው ታሪክ አንድን ሕዝብ የራሱ ዘር ከሌላው ዘር በከፋ መልኩ በድሎት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ግን ገዥዎችን እንጂ ህዝብን የሚመለከት ጉዳይ አይደለም፡፡
የትምክህትና የጥበት ኃይሎች ያለፉትን የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶችን በማንሳት አንድን ህዝብ ለመኮነን ሶሞክሩ ይስተዋላል። ይህ ፍፁም ከዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሳቤ ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ ዛሬ ላይ የአንድ ብሔር የበላይነት በሌለበት ሁኔታ፣ እንዲህ ዓይነቶቹን የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን በማጋጋም ትርፍ ለማግኘት መሞከር ተገቢነት የለውም። ይህን ለማስረጽ የሚሞክር ካለም አይሳካለትም። ለምን? ቢባል እየተካሄደ ያለው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሳቤ ውጤት እያስገኘ ከመሆኑ በላይ፣ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት በሚደረገው ርብርብ ላይ ቁልፍ መሣሪያ ሆኖ በመቀጠሉ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን እንዲያብብም ወሣኝ ሚና እየተጫወተም ስለሆነ ነው፡፡
ያም ሆኖ ይህ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን መጠናከር መሠረት የሆነው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ከአራት መሠረታዊ ትርጓሜዎች አኳያ መመልከት ይቻላል። አንደኛው ማንነትን ማወቅ ነው። ሁለተኛው የሌሎች ማንነትን ማወቅ ነው። ሦስተኛው እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው። አራተኛው ደግሞ አካባቢን ማልማት ነው። ማንነትን ከማወቅ አኳያ የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥቅሞችን መለየት ይገባል።  የጋራ የሆኑ ባህሪያትን መለየትንም እንዲሁ። የሌሎችን ማንነት በማወቅ በኩልም፣ ከሌሎች ጋር ያለውን የጋራ ፍላጎትና ጥቅም መለየት ተገቢ ይሆናል።  
እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም የጋራ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመብለጥም ሆነ በማነስ ስሜት ውስጥ ሳይገባ በጋራ መጠቀም ተገቢነት አለው። አካባቢን ከማልማት አንጻርም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ አካባቢን በተገቢው መንገድ ለልማት ማዋል ይገባል። የእነዚህ ድምር ውጤትም ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን በመፍጠር ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ያጠናክራል።
ባለፉት ዓመታት እነዚህን ሁኔታዎች ከህገ መንግሥቱ አኳያ በመመልከት በርካታ በጎ ተግባራት ተከናውነዋል። የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም በህገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡትን የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሳቤዎችን ገቢራዊ ለማድረግ ተችሏል። ይህ ሁኔታም ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲጠናከር በር ከፍቷል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እውን በሆነበት አገር ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ማበቡ አይቀሬ ነው።  በመሆኑም ባለፉት 23 ህገ መንግሥታዊ ዓመታት ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲያብብ ጥረት ተደርጓል። ይህ ሁኔታ ይበልጥ እንዲጎለብት የዴሞክራሲያዊ አንድነት መሠረቱ የሆነውን የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ማክበርና ማስከበር ይገባል።
ዴሞክራሲያዊ አንድነቱ የተጠበቀ የየትኛውም አገር ህዝብ ያለመውን ሁለንተናዊ ዕድገት ተፈጻሚ ማድረጉ አይቀርም። ከኢትዮጵያ አኳያም በአገሪቱ ውስጥ እየተፈጠረ ባለው ዴሞክራሲያዊ አንድነት ሣቢያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህዳሴያቸውን ለማረጋገጥ የሰነቁትን ራዕይ ገቢራዊ እያደረጉ ነው። በመሆኑም ላለፉት 15 ዓመታት ወደ ህዳሴያቸው በሚወስዳቸው ጎዳና ላይ መጓዝ ይዘዋል።
ዴሞክራሲያዊ አንድነታችንን አፅንተን በህገ መንግሥታችን ጥላ ስር እንሰባሰብ። እናም ህገ መንግሥታችን የዴሞክራሲያዊ አንድነታችንና የህዳሴያችን መሠረት በመሆኑ ሁሌም እንኮራለን። እንዘክራለንም።