የኬንያ መንግሥት የወጪ ንግዱን ለማሳደግ የሚያስችል ብሔራዊ ንግድ ፖሊሲ ይፋ አደረገ

የኬንያ መንግስት ሀገሪቱ ወደ ውጪ የምትልካቸውን ምርቶች ለማስፋት የሚያስችል ብሔራዊ የንግድ ፖሊሲ ይፋ ማድረጉን  አስታወቀ፡፡

ብሔራዊ ንግድ ፖሊሲ እ.ኤ.አ በ2022 ኬንያ ወደ ውጪ የምትካቸውን ምርቶች  በየአመቱ በ20 በመቶ ለማሳደግ ያለመ መሆኑንም ተገልጻል፡፡

የኬንያ መንግስት የሀገሪቱን የውጭ ንግድ ለማሳደግና ምርቶቹን በመላው አለም ለማስተዋወቅ  የሚያስችል እቅድ ነድፎ ወደ ስራ ለመግባት መዘጋጀቱን ነው የተገለጸው፡፡

አዲስ የተረቀቀው የንግድ ፖሊሲ ኬንያ እኤአ በ2022 ወደ ውጪ የምትልከውን ምርት በየአመቱ በ20 በመቶ ለማሳደግ ያለመ መሆኑንም የሀገሪቱ ንግድ ሚኒስቴር ፀሀፊ ክሪስ ኪፕቶ ተናግረዋል፡፡

ፀሀፊው አያይዘውም እቅዱ  የሻይ ፤ የቡና ፤ የአበባ    የትንባሆ ፤   የጨርቃጨርቅ እና የአልባሳት  ምርቶችን  ላይ የሚያተኩር ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ሀገሪቱ ወደ ውጪ በምትልካቸው ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር የውጭ ንግዷን ለማስፋት እድል እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡

በዚህም በአውሮፓ ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸውን የቀዘቀዙ አትክልቶችን እንዲሁም ከሌሎች የአለም ክሎች ይልቅ በይበልጥ በሳውዲ አረቢያና በግብጽ ተፈላጊነት ያላቸው የስጋ ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ ለማቅረብም በቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ እንደሚገኙ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ኪፕዮቶ ኬንያ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ  የምትችልበት ሰፊ  ዕድል እንዳላት ገልጸው  ለዚህ እድል መቃናትም  ወደ ውጭ አገራት በምትልካቸው ምርቶች ላይ የተጠናከረ ሥራ ማከናወን  ይጠበቅባታል ሲሉ አስታወቀዋል፡፡

በኬንያዋ ዋና ከተማ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩትም  አዲስ የተዘረጋው ስትራቴጂ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል ግልጽ መንገድ እንዲኖረን ያስችለናል ብለዋል፡፡

ሀገሪቱ እኤአ በ2022 የውጭ ንግዷን በ20 በመቶ ለማሳደግ የያዘችውን እቅድ ለማሳካትና ምርቶቿን ለመቀበል አቅም አላቸው ያለቻቸውን 12 ሀገራት ለይታለች፡፡

 

እነዚህ ሀገራትም ኡጋንዳ ፤ ታንዛኒያ፤ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፈ ኮንጎ ፤ ግብጽ ፤ ሩዋንዳ ፤ ደቡብ ሱዳን ፤ ጀርመን ፤ እንግሊዝ ፤ ፓኪስታን፤ ሆላንድ እና አሜሪካ ናቸው፡፡

 

ኬንያ ከታንዛኒያ ጋር ያላትን ወቅታዊ ሁኔታ ወደ ጎን በመተው ሀገሪቱን እንደ ዋና የገበያ መዳረሻ አድርጋ መውሰድን መርጣለች፡፡ ይህም የመጣው አገሪቱ ከአለም ስድስተኛ ከምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት መካከል ደግሞ ከከኡጋንዳ በመቀጠል ሁለተኛ ወሳኝ  የንግድ አጋሯ በመሆኗ ነው፡፡

ኪፕቶ አክለውም ሀገሪቱ ምርቶቿን በምታቀርብባቸው የአለም ሀገራት ላይም የተጠናከረ ስራ ለመስራት በዝግጅት  ላይ መሆኗን  ተናገረዋል፡፡ ለምሳሌም ኬንያ 13 በመቶ የሚሆነውን   የውጭ ምርቶች ወደ ሀገሯ ከምታስገባባት ቻይና የአንድ በመቶ የውጭ ንግድ ድርሻ ብቻ ነው ያላት፡፡

ኬንያ ወደ ህንድ የምትልከው ምርት በተመሳሳይ የ 1 በመቶ ድርሻ ብቻ ያለው ሲሆን ከሀገሪቱ የምታስገባው ምርት ግን 12 በመቶ ይደርሳል፡፡

ይህ ልዩነትም ኬንያ አዲስ ያወጣችውን የንግድ ፖሊሲ ላማሳካት ያግዛታል ተብሏል፡፡

የኬንያ ስታቲስቲክስ ቢሮ መረጃ እንዳመላክተው ከሆነ እ.ኤ.አ በ 2016 ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባቸው ምርቶች በ9ነጥብ3 በመቶ ያቀነሱ ሲሆን ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች ደግሞ በ3ነጥብ1 ቢሊዮን ሺሊንግ ቅናሽ አሳይተዋል፡፡

አዲሱ የውጭ ንግድ ስትራቴጂ ከ2 ወራት በኃላ እኤአ በ2018 ጥር ወር ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ኢስት አፍሪካን ዶት ኮም አስነብቧል፡፡