ህዳር 29፤ የእኩልነት፣ የአንድነትና የወንድማማችነት ቀን

በያዝነው ወር ማብቂያ ላይ ማለትም ህዳር 29፣ 2010 ዓ/ም 12ኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰመራ ከተማ ላይ ይከበራል።   የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በየዓመቱ በአንድ አካባቢ ከተማ ወይም ክልል አይደለም የሚከበረው። ክልሎች እየተፈራረቁ ነው የሚያከብሩት። ዘንድሮ በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የሚከበረውን ጨምሮ እስካሁን ዘጠኙም ክልሎች የብሄሮ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንን የማስተናገድ እድል አግኝተዋል። አዲስ አበባ ከተማ ሁለት ጊዜ ያህል እድሉን አግኝታለች። ምናልባት አሁን በአሉን የማክበር እድል አላገኘም ሊባል የሚችለው የድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ብቻ ነው።

የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን የሚከበርበት ህዳር 29 የኢፌዴሪ ህገመንግስት የጸደቀበት ዕለት ነው። የኢፌዴሪ ህገመንግስት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ሆነው በእኩልነት ላይ በተመሰረተ አንድነት ለመኖር የገቡት የቃል ኪዳን ሰነድ ነው። በኢፌዴሪ ህገመንግስት የተመሰረተችው አዲሲቱ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል እንደነበሩት አሃዳዊ ሥርአቶች በሃይል የተመሰረተና በሃይል የሚጠበቅ የወሰን/የመሬት አንድነት ሳይሆን የህዝቦች አንድነት ያላት ሃገር በመሆኗ ህገመንግስቱ የኢትዮጵያ አንድነት የተቋጠረበት ውል ነው። ህገመንግስቱ እስካለ ድረስ የኢትዮጵያ አንድነት ይቀጥላል። ህገመንግስቱ ከፈረሰ ግን የአንድነቱ ውል ተፈትቶ ኢትዮጵያ ትፈራርሳለች።

የኢፌዴሪ ህገመንግስት ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሌላ አካል ተዘጋጅቶ የተሰጠ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአንድነት ለመኖር ያስችለናል በሚል መክረው፣ ዘክረው፣ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ያጸደቁት የስምምነት ወይም የቃል ኪዳን ሰነድ ነው።

ኢትዮጰያ ከ80 በላይ የተለያየ ማንነት – ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግና ልማድ፣ ታሪክ፣ . . . ያላቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያ ብትሆንም ለእኒህ የተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሃገር አልነበረችም። ዘውዳዊውና ወታደራዊው አሃዳዊ የመንግስሥት ሥርአቶች ለብሄራዊ ማንነታቸው ለቋንቋቸው፣ ለባህላቸው፣ ለታሪካቸው ዕውቅና ነፍገው የዜግነትና ሰብአዊ መብቶቻቸውን ነፍገዋቸዋል።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት ማግኘት አይችሉም ነበር። ፍርድ ቤት ቆመው ጉዳያቸውን ምንም በማያዳምጡትና ራሳቸውን መግለጽ በማይችሉበት ቋንቋ እንዲሟገቱ ይገደዱ ነበር። ህጻናት ምንም ሊግባቡ በማይችሉበት ቋንቋ ለመማር ይገደዱ ነበር። ከሥርአቱ ቋንቋና ሥርአቱ እወክለዋለሁ ከሚለው ብሄራዊ ማንነት ውጭ የሆኑ ማንነቶች በሙሉ እንደርካሽ እንዲቆጠሩ ዘመቻ ተካሂዶ ነበር። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በማንነታቸው እንዲሸማቀቁና አንገታቸውን እንዲደፉ ለማድረግ ሥትራቴጂ ተነድፎ ተግባራዊ ተደርጓል። የያኔው ኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ማንነትን የማይቀበል ነበር።

በኢትዮጵያ የሚኖሩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህን ከእነብሄራዊ ማንነታቸው ዜግነት ሊሰጣቸው ያልፈቀደ ሥርአት በጸጋ አልተቀበሉትም። ብረት አንስተው ተዋግተውታል። የህይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል። በመጨረሻም ላይመለስ ከስሩ ነቅለው አስወግደውታል። የመጨረሻውን አምባገነን መንግስት በትጥቅ ትግል ሲወጉ የነበሩ በብሄር የተደራጁ የነጻነት ንቅናቄዎች ከሃያ በላይ እንደነሩ ልብ ይሏል።

በየራሳቸው ለነጻነት የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የነበሩ ብሄራዊ የነጻነት ንቅናቄዎች የመጨረሻው አሃዳዊ ሥርአት የነበረው ወታደራዊ ደርግ ከተወገደ በኋላ፣ ከሁለት አማራጮች ጋር ተፋጠጡ። አንደኛው የየራሳቸውን ነጻ መንግስት መመስረት ሲሆን ሁለተኛው ብሄራዊ መብትና ነጻነታቸው ሳይሸራረፍ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነት የሚኖሩበት አንድ የጋራ ሃገር መመስረት ነበር። ከእነዚህ ሁለት አማራጮች ሁለተኛውን ማለትም ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነት የመኖርን አማራጭ ለመሞከር ተስማሙ።

እናም ወታደራዊው ደርግ በወደቀ ማግስት ማለትምመ ሰኔ 24፣ 1983 ዓ/ም ቀጣይ እጣ ፈንታቸውን ለመወሰን በአንድ አዳራሽ ጉባኤ ተቀመጡ። በዚህ ጉባኤ ላይ ከ30 በላይ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ብሄራዊ የነጻነት ንቅናቄዎችና ሌሎች በውጭ ሃገር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እንዲሁም ደርግ ከተወገደ በኋላ በአንድ ወር እድሜ ውስጥ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ ነበሩ። በዚህ ጉባኤ ላይ የመበታተኑን አማራጭ ተተው አብረው ለመኖር ተስማሙ። አብረው መኖር የሚያስችላቸውን የቃል ኪዳን ሰነደም ለማዘጋጀት ተስማሙ።

ይህን አብረው ለመኖር የሚያስችላቸውን የቃል ኪዳን ሰነድ በሚያዘጋጁበት ጊዜ ሃገሪቱን የሚያስተዳደር ሁሉም የሚሳተፉበት የሽግግር መንግስት መሰረቱ። የሽግግር መንግስቱ እንደ ህገመንግስት ሲገለገልበት የነበረው ሁሉም ፓርቲዎች መክረው ያጸደቁት ቻርተር የብሄሮችን፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል ያከበረ ነበር። ያም ሆነ ይህ የሽግግር መንግስቱን ሲያስተዳደር የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች የተወከሉበትና በገለልተኛ እውቅ ባለሞያዎች የሚታገዝ የህገመንግስት አርቃቂ ኮሚሽን መሰረቱ። ይህ የሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ውክልና የተንጸባረቀበት ኮሚሽን የህገመንግት ረቂቅ አዘጋጀ። በዚህ የመጀመሪያ ረቂቅ ህገመንግስት ላይ ለአካለ መጠን የደረሱ የሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አባላት የሆኑ ዜጎች እንዲወያያበት ለህዝብ ተመራ። ዜጎች በረቂቅ ህገመንግስቱ እያንዳንዱ አንቀጽ ላይ በመወያየት መቀነስና መታከል አለበት ያሉትን አያይዘው መልሰው ለኮሚሽኑ ላኩ። ኮሚሽኑ ህዝብ በሰጠው አስተያየት መሰረት ረቂቁን አዳብሮ ለሁለተኛ  ጊዜ ወደህዝብ መራው። ህዝብ ልክ እንደመጀመሪያው ረቂቅ ሁሉ አንቀጽ በአንቀጽ ተወያይቶ ማሻሻያዎችን አክሎ ላከው። ረቂቁ ለሁለተኛ ጊዜ በዚህ የህዝብ ማሻሻያ አስተያየት መሰረት እንዲዳብር ተደረገ።

ይህን በህዝብ የዳበረ ህገመንግስት የማጽደቅ ተግባር አሁንም ለህዝብ ነው የተተወው። የኢትዮጵያ ህዝብ አሳታፊ፣ ግልጽ፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ በሆነ፤ በምስጢር ድምጽ በተሰጠበት ሥርአት የህገመንግስት አጽዳቂ ምክር ቤት አባላትን መረጠ። ይህ በህዝብ የተወከለ የህገመንግስት አጽዳቂ ምክር ቤት እያንዳንዱ የረቂቅ ህገመንግስቱ አንቀጽ ላይ እየተወያየ በአብላጫ ድምጽ እያሳለፈ በመጨረሻ የኢፌደሪን ህገመንግስት አጸደቀ። ይህ ህገመንግስት ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ የሉአላዊ ሥልጣን ባለቤት ሆነው በአንድ ፌደራላዊ ሥርአት ስር ለመኖር የተስማሙበት የቃል ኪዳን ሰነድ ነው። ይህ በህገመንግስቱ መግቢያ ላይ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል። ይህ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አብሮ የመኖር የቃል ኪዳን ሰነድ በይፋ የጸደቀው ህዳር 29፣ 1987 ዓ/ም ነበር። የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በየዓመቱ በዚህ ዕለት አንዲከበር የተወሰነው ለዚህ ነው።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ የሆነው የኢፌዴሪ ህገመንግስት የጸደቀበትን ዕለት መነሻ በማድረግ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ዓላማ በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነት ማጠናከር ነው። ዕለቱ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማንነታቸውን – ባህላቸውን በሚያንጸባርቅ አኳሆን በአንድ ቦታ ተሰባስበው አንዱ ሌላውን የሚያውቅበትን እድል በመፍጠር ወንድማማቭችነትን ያጠናክራል።

ይህ በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሃከል ወንድማማችነትን የሚያጠናክር ሁነት ማዘጋጀት ህገመንግስታዊ መሰረት ያለው ጉዳይ ነው። የኢፌዴሪ ህገመንግስት መንግስት በብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሃከል ወንድማማችነት የመፍጠር ሃላፊነት እንዳለበት ይገልጻል። ህገመንግስቱ በአንቀጽ 88 ፖለቲካዊ ነክ ዓላማዎች በሚል ርዕስ ስር በንኡስ አንቀጽ 2 ላይ መንግስት፣ የብሄሮችን፣  ብሄረሰቦችን፣ የህዝቦችን ማንነት የማጠናከር በዚሁ ላይ በመሞርከዝ በመካከላቸው እኩልነት፣ አንድነትና ወንድማማችነት የማጠናከር ግዴታ አለበት ይላል። ይሄው ድንጋጌ በሁሉም ክልሎች ህገመንግስቶችም ላይ ሰፍሮ ይገኛል። በየዓመቱ ህዳር 29 የሚከበረው የብሄሮች፣ የብሄረሰቦችና ህዘቦች ቀን የዚህ ህገመንግስታዊ ድንጋጌ ተግባራዊነት አንዱ መገለጫ ነው።