ግብርናን የሚመግብ ኢኮኖሚ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በግብርና ላይ የተመሰረተ ነው። ኢኮኖሚው ግብርና ላይ የተመሰረተ መሆኑን የሚያመለክቱት፣ በዘርፉ ላይ ኑሯቸው የተመሰረተ ዜጎች መጠን፣ ዘርፉ የሃገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ ገቢ ውስጥ ያለው ድርሻ፣ በወጪ ንግድ ውስጥ ያለው ድርሻና ለሃገሪቱ አጠቃላይ እድገት የሚያበረክተው ድርሻ ናቸው።

ግብርና 80 በመቶ የሚሆነው የሃገሪቱ የሰው ሃይል የተሰማራበት ዘርፍ ነው። ይህን ያህል የሃገሪቱ ዜጎች ኑሮ የተመሰረተው በግብርና ነው። የግብርና ዘርፍ እድገት መቀጨጭ፣ ወይም ማሽቆልቆል በሃገሪቱ ዜጎች ህይወት መቀጨጭና ማሽቆልቆል ይገለጻል። ቀደም ባሉት ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ የኑሮ መገለጫ እጅግ አስከፊ ድህነት የሆነው ከ80 በመቶ በላይ የሃገሪቱ ህዝብ የኑሮ መሰረት የሆነው ግብርና አርሶ አደሩን እንኳን መመገብ የማይችል ኋላ ቀር በመሆኑ ነበር። በአጠቃላይ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ ከፍተኛ የነበረው ግብርና የተሰማራበትን አርሶ አደር እንኳን መመገብ የማይችል፣ ምንም ትርፍ ምርት የማይፈጠርበት መሆኑ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች እንዲያቆጠቁጡና እንዲያድጉ የሚያግዝ ሃገራዊ የካፒታል ክምችት መፍጠር እንዳይቻል አድርጓል። የሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ምንጭም ይሄው የግብርና ዘርፍ በመሆኑ የሃገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት እንዲቀጭጭ ምክንያት ሆኗል።  

በኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በአጠቃላይ ሃገራዊ ምርት ውስጥ የነበረው ድርሻ ከሁሉም የላቀ ነበር። እርግጥ ይህ ሁኔታ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ በተለይ በአገልግሎት ዘርፎ የተበለጠበት ሁኔታ ታይቷል። ይህ የሆነው የግብርናው እድገት አሽቆልቁሎ ወይም በነበረበት ተገትቶ ሳይሆን የአገልግሎት ዘርፉ የበለጠ እድገት በማሳየቱ ነው። በአሁኑ ወቅት ግብርና የሃገሪቱ አጠቃላይ ምርት ውስጥ 36 ነጥብ 3 በመቶ ገደማ ድርሻ አለው። የአገልግሎት ዘርፍ 39 ነጥብ 3  በመቶ ድርሻ ሲኖረው የኢንደስትሪ  ዘርፉ ድርሻ 25 ነጥብ ነጥብ 6 በመቶ ነው። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ከአመታት በፊት መሪው ግብርና ነበር።

የግብርናው ዘርፍ በሃገሪቱ የወጪ ንግድ ውስጥ ያለው ድርሻ አሁንም በጉልህ ከፍተኛ ነው። ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመም፣ አበባና የቁም ከብት የመሳሰሉት የግብርና ምርቶች 80 በመቶ የሃገሪቱን የወጪ ንግድ ይሸፍናሉ። የግብርናው ዘርፍ አሁንም በተሰማራበት የሰው ሃይልና በወጪ ንግድ ድርሻ ቀዳሚ ነው።  በሃገሪቱ የዜጎችን ህይወት ለማሻሻልና ለሌሎች ዘርፎች መጎልበት የሚያግዝ የካፒታል ክምችት በመፍጠር ሂደት ውስጥ ግብርና የማይተካ ሚና አለው። በመሆኑም አሁንም የግብርና ዘርፍ ልማት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የግብርናውን ዘርፍ ችላ ብሎ የኢንደስትሪና የአገልግሎት ዘርፉን ማሳደግ አይቻልም። በተጨባጭ ሃገራዊ የካፒታል ክምችት መፍጠር የሚያስችለው ዘርፍ ግብርና ነው። ባለፉት አንድ ተኩል አስርት ዓመታት ውስጥ የተመዘገበው አጠቃላይ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥም ግብርና ከፍተኛ ድርሻ ነበረው። የግብርናው ዘርፍ ልማት ትኩረት ባይሰጠው ኖሮ አጠቃላይ እድገቱ፣ በተለይ በኢንደስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች የተመዘገበው እድገት ከእቅድ ያለፈ ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም ነበር።

ባለፉት ሶስት ዓመታት የግብርናው ዘርፍ እድገት መለስ ብለን እንመልከት። በ2008 በጀት ዓመት የግብርና ዘርፍ ከባለፉት አንድ አስርት ዓመታት ሁሉ  አነስተኛ እድገት ያስመዘገበበት ዓመት ነበር። በ2008 ዓ/ም ግብርና የ8 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ማደግ የቻለው ግን በ2 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ ነበር። የዚህ ምክንያት በ2007 ዓ/ም በልግና ክረምት በተለያየ የሃገሪቱ አካባቢዎች በኤል ኒኖ ሳቢያ የተፈጠረ ድርቅ ነው። በ2009 ዓ/ም የግብርናው ዘርፍ እድገት ማገገም አሳይቷል። በ2009 ዓ/ም የግብርናው ዘርፍ በ8 በመቶ ያድጋል ተብሎ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የ6 ነጥብ 7 በመቶ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል። በያዝነው ዓመት ማለትም በ2010 በጀት ዓመት የግብርና ዘርፍ በ8 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል። እስካሁን በማሳና በምርት ስብሰባ ትንበያ የተገኘ መረጃ የእድገት እቅዱ ሊሳካ እንደሚችል ያመለክታል።

ከዘንድሮ የመኸር ምርት በአጠቃላይ 345 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት እንደሚጠበቅም የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታውቋል። የሃገሪቱ መኸር አብቃይ አከባቢዎች የተስተካከለ የዝናብ ስርጭት ስለነበረ፣ ማሳ ላይ ጥሩ ሰብል መኖሩንና አሁን በአብዛኛው የተሰበሰበውን ምርት መነሻ በማድረግ ዘንድሮ 345 ሚሊየን ኩንታል ሰብል ይመረታል ተብሎ ይጠበቃል። ባለፈው ዓመት ከመኸር እርሻ የተሰበሰበው አጠቃላይ ምርት 292 ሚሊየን ኩንታል ነበር።

የግብርናው ዘርፍ ላይ እየታየ ያለው እድገት ምንጭ የአርሶ አደሩ የተሻለ የምርት ግብአትና ማዳበሪያ የመጠቀም ልምድ መሻሻል፣ እንዲሁም ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ጉልህ ድርሻ ካለው የመስመር እርሻ ስልት ጋር መለማመድ እንዲሁም ብጥስጣሽ እርሻ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ለማስቀረት በርካታ ኩታ ገጠም ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች በተያያዘ ሰፊ ማሳ ላይ ማምረት መጀመራቸው ነው። በባህላዊ የምርት ስብሰባ ወቅት የሚባክነውን እስከ 30 በመቶ የሚደርስ ምርት ለመቀነሰ አነስተኛና ከፍተኛ የምርት ስብሰባ ሜካናይዜሽን የመጠቀም ልምድ መሻሻል በማሳየቱም ለምርታማነት እድገት አስተዋጽኦ አበርክቷል።

አሁን የአርሶ አደሩ ምርታማነት በእጅጉ መሻሻል አሳይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም በቅርቡ በአማራ ክልል ያለውን የምርት ስብሰባ በጎበኙበት ወቅት በሰጡት መግለጫ፣ አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም በአንድ ሄክታር መሬት ከስድስት እስከ ስምንት ኩንታል ስንዴ ያመርት እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት በግብርና ሜካናይዜሽን በመታገዝ በሄክታር በአማካይ 64 ኩንታል ለማምረት መቻሉን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ምርት ላይ የሚታየው ሌላው ችግር በዝናብ ላይ ጥገኛ መሆኑ ነው። ይህ ሁኔታ የዓመቱን የምርት ወቅት ከመገደቡ በተጨማሪ እያሰለሰ ሃገሪቱን በሚያጋጥማት ድርቅ በሚሊየን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን ለምግብ ተረጂነት እስከማጋለጥ የሚደርስ የምርት ማሽቆልቆል ያስከትላል። ይህ የምርት ማሽቆልቆል የሃገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይም ጉልህ ተጽእኖ ያሳድራል። ባለፉ አስር ዓመታት በአማካይ 8 በመቶ እድገት ሲያሳይ የቆየው ግብርና በ2007 በተከሰተው ኤል ኒኖ ያስከተለው ድርቅ ሳቢያ እድገቱ ወደ 2 ነጥብ 3 ማሽቆልቆሉን ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል።

ይህን ችግር ለመቋቋም ለመስኖ እርሻ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል። የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በ2009 በጀት ዓመት በሃገሪቱ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ለምቷል። ከዚህ የመስኖ ልማት ከ370 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል። በዚህም 7 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነው የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ችለዋል።

ዘንድሮም በተመሳሳይ  ከ7 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮችን በመስኖ ልማት ፕሮግራም የማሳተፍ እቅድ ተይዟል። እነዚህ አርሶ አደሮች በዓመቱ ደረቃማ የበጋ ወራት በመስኖ ልማት ላይ የሚሰማሩ ናቸው። በመስኖ ፕሮግራሙ 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት ይለማል ተብሎ ይጠበቃል። አሁን የደረሱ ሰብሎች በተሰበሰቡባቸው አካባቢዎች የመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት ፕሮግራም መካሄድ ጀምሯል። እስካሁን 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬቱ በመስኖ ልማት መርሃ ግብር በሰብል መሸፈኑንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል። ከዘንድሮ የመስኖ ልማት 450 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል። የመስኖ ልማት ምርቶች በአመዛኙ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። እርግጥ የአገዳ ሰብሎችም በመስኖ ይለማሉ።

በሌላ በኩል በተያዘው በጀት ዓመት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ  ሰባት ለመስኖ ልማት የሚውሉ የግድብ ፕሮጄክቶች ወደ ልማት ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ  የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታውቋል። እነዚህ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች ተንዳሆ፣ ከሰም፣ ርብ፣ አልዌሮ፣ ቆጋ፣ መገጭና ጎዴ አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው። ወደ ልማት እየገቡ ያሉት ፕሮጀክቶች በተለይ  ለስኳር ልማት የሚውሉ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በፕሮጀክቶቹ አካባቢዎች የሚገኙ አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮችን ከዝናብ ጥገኝነት ያላቅቃል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ባለፈ ለበጋ ወራት የእርሻ ስራ እንዲሁም የመጠጥ  ውሃ  ፍላጎትን የማሟላት አቅም አላቸው።

በአጠቃላይ ከላይ የጠቀስናቸው መረጃዎች በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ላለው የግብርና ልማት አሁንም ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ያመለክታሉ። በዘርፉ  የተሰማራውን አብዛኛውን የሃገሪቱን ህዝብ ማኖር፣ ኑሮውን ማሻል የሚያስችለው የግብርና ዘርፍ የሃገሪቱ የካፒታል ክምችትና የውጭ ምንዛሪ ምንጭም ነው። የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ግብርናን እየተመገበ የሚያድግና የሚሸጋገር (transform) በመሆኑ ዘርፉ እያሳየ ያለው እድገት አጠቃላይ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ እድገትና ሽግግር አቅጣጫ ባለተስፋ መሆኑን ያመላክታል።