በኡጋንዳ የሚገኙ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ነሯቸውን ለማሻሻል ጥረት እያደረጉ ነው

በኡጋንዳ ያሉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በአነስተኛ የንግድ ዘርፍ  በመሰማራት ለኑሮአቸው መሻሻል ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ተገለጸ፡፡ 

የሀገሪቱ ዜጎችም ስደተኞቹ በሠፈሩበት አካባቢ በንግድ ዘርፍ በመሠማራት ውጤታማ መሆናቸው ተነግሯል፡፡ 

የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን ተቀብለው ከሚያስተናግዱ ግንባር ቀደም  ከሆኑት ጎረቤት ሀገራት መካከል የምትገኘው ኡጋንዳ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስደተኞችን እያስተናገደች ትገኛለች፡፡

ከኡጋንዳ ከተሞች ደግሞ ፓሎሪኒያ ከ20ሺህ በላይ ስደተኞችን  በማስተናገድ ትታወቃለች።

የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ በመሆኑ ስደተኞቹ ተጠልለው ባሉበት ሀገር ኑሮአቸውን በድጋሚ ለመቋቋም እየተፍጨረጨሩ ይገኛሉ፡፡

በኡጋንዳ ያሉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችም በአነስተኛ የንግድ ዘርፍ  በመሰማራት ኑሮአቸውን ለመምራት የተቻላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው ።

ስደተኞቹ በቦታው በደረሱበት ወቅት በተቋቋመው የገበያ ሥፍራ የሀገሪቱ ዜጎች እና በስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ተጠልለው የሚኖሩ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች የተለያዩ ምርቶችን ግብይት የሚያካሄዱበት ሥፍራ  ተዘጋጅቷል ፡፡

ያንዱክ ኤክ በደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነቱን በመሸሽ ወደ ኡጋንዳ ከቤተሰቦቿ ጋር በመሆን እኤአ በ2015 መሰደዷን ትናገራለች ።  

ኤክ እና ጓደኛዋ በስደት ባሉባት ሀገር ኡጋንዳ ኑሮአቸውን ለማሸነፍ የአሳ ፤ የቲማቲም እና የሽንኩርት ንግድ ላይ መሰማራታቸውን ይገልጻሉ ፡፡ በዚህም የእለት ኑሮአቸውን ከመሸነፍ አልፈው የተመጣጠነ ምግብ ለመመገብ መብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሱሳን ኤኮሩ ኡጋንዳዊ ዜግነት የተሠጣት ደቡብ ሱዳናዊት ስትሆን ባለፈው አመት ከመንግስት ባገኘችው 3 ሚሊየን ሽሊንግ ወይም 870 የአሜሪካን ዶላር ብድር ስደተኞቹ በሰፈሩበት አካባቢ በነዳጅ ሽያጭ ተሰማርታ ውጤታማ መሆኗን ተናግራለች፡፡

ከመንግስት ያገነችውን ብድር በአንድ አመት ከስድስት ወር ውስጥ በመመለስ በራሷ ገንዘብ ንግዷን እያካሄደች መሆኗን ገልጻለች፡፡ ምንም እንኳን የባህል ልዩነት ቢኖርም የአካባቢው የህብረተሰብ ክፍሎች ከስደተኞቹ ጋር ተግባብተው  እንደሚኖሩም ተናግራለች፡፡

ጎድፍሬይ ባይሩሃንጋ የፓሎሪኒያ የስደተኛ ጣቢያ አስተዳዳሪ የስደተኛ ማቆያ ጣቢያው እ.አ.አ በ2016 ታህሳስ ወር ላይ ስራ እንደጀመረ አስታውሰው የስደተኞቹ በአካባቢው መስፈር ለአካባቢው ህብረተሰብ የኑሮ መሻሻል አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

አነስተኛ ሆስፒታል እና ትምህርት ቤት በአካባቢው በመከፈቱም ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ይህ የገበያ ስፍራ እና መሰል የጥቃቅን የንግድ ተቋማት በስደተኛ ጣቢያዎች አካባቢ መስፋፋት የሚበረታታ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን  ስደተኞችም በመጠለያ አቅራቢያቸው በመሰል እንቅስቃሴዎች ላይ በመሳተፍ ከሌሎች አካላት ድጋፍን ከመጠበቅ ይልቅ እራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር እድል እንደሚፈጥርላቸው ተገልጻል፡፡ 

የተጀመረውን ስራ አጠናክሮ በመስቀጠል ስደተኞች እራሳቸውን እንዲያቋቁሙና ኑሮአቸውን እንዲደጉሙ ከመንግስና ከተለያዩ አካላት  ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተመልክቷል ።( ምንጭ: ጉርቶንግ)