ሙያዊ ክሂሎትና የግብርናው ዘርፍ

ለሀገራችን ወሳኝ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ከሚያስመዘግቡት ዘርፎች ውስጥ ዋነኛ መሰረት የሆነው የግብርናው ዘርፍ ነው፡፡ ግብርናችንን ፍጹም ኋላቀር ከሆነ የአስተራረስ ዘዴና አጠቃቀም በማውጣት ዘመናዊ ወደሆነ የእርሻ መስክ ለመለወጥ፤ አርሶአደሩንም ሆነ አርብቶአደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ፤ እንዲሁም ሀገራዊ ምርትን በከፍተኛ መጠን ለማሳደግ ይቻል ዘንድ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ግብርና ሚኒስቴር ባሰማራቸውና በተለያዩ የግብርናው ዘርፎች ሰፊ እውቀት ባላቸው ባለሙያዎች አማካኝነት አርሶአደሩ የዘመናዊ እውቀት ባለቤት እንዲሆን ጥረት ተደርጓል፡፡ በግብርናው ምርት እድገት፣ በአፈር ጥበቃና መስኖ ስራዎች፣ በአካባቢ እንክብካቤና ጥበቃ ወዘተ እጅግ የላቁ ውጤቶችንም ለማግኘት ተችሎአል፡፡ በእውቀት ማነስ ምክንያት ለዘመናት ሲጨፈጨፍና ሲራቆት የቆየው ደናችን፤ በአሁኑ ሰአት በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቀድሞ ወደነበረበት የተፈጥሮ ውበት መመለስ ችሎአል፡፡ ሀገራዊው የግብርና ልማትም በተፋጠነ መልኩ እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን በታሪክ ውስጥ ያልነበሩ መሰረታዊ ለውጦችን ለማስመዝገብ በቅቶአል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው አርሶአደሩን በግብርና አሰራር እጅግ ኃላቀር ከሆነው የዘልማዳዊ አስተራረስ በማውጣት ዘመናዊ እውቀት እንዲያገኝ በስራ ላይም እንዲያውለው በመደረጉ ነው፡፡

ሀገሪቱ ለምትገነባቸው ዘመናዊ፣ ከባድና ቀላል እንዱስትሪዎች መሰረታዊ ግብአቶችን የሚያቀርበው የግብርናው ዘርፍ ደረጃ በደረጃ ወደ ግብርና ሜካናይዜሽን የሚለወጥበት ሰፊ ስራም እየተሰራ ይገኛል፡፡ በሀገራችን በቀላሉ በግለሰብ አርሶ አደር የሚንቀሳቀስ ማረሻ ከመስራት ጀምሮ በመኪና መልክ የእርሻ ስራን የሚያከናውኑ ሰብል መዝሪያ፤ መሰብሰቢና መውቂያ ማሽኖችን መስራት የተቻለበት ደረጃ ላይ የደረስን በመሆኑ የወደፊቱ የግብርና እርሻና ውጤቶቻችን ከፍተኛ ስርነቀል ለውጦችን እንደሚያስገኙ በእርግጠኝት መናገር ይቻላል፡፡

 

ይህም ብቻ ሳይሆን ሌሎች፣ የግብርና ስራችንን የበለጠ የሚያጎለብቱ በርካታ ስራዎች በስፋት በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ ሕብረተሰብ አቀፍ የተቀናጀ የስነ ምሕዳር ጥበቃና የመሬት ልማት አስተዳደር ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ የአካባቢ ደን ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ማስታወቁም ከዚሁ ጋር አብሮ የሚገለጽ ነው፡፡ በሚኒስቴሩ ዘላቂ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ ዶ/ ተስፋዬ ኃይሌ ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን እንደገለጹት ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ የኢኮኖሚ ግንባታን ከዳር ለማድረስ በማለም እየተሰራ ያለ ስራ ነው፡፡

 

የፕሮጀክቱ ዓላማ የብዝሐ ሕይወት ኃብቱ በሀገሪቱ የልማት እድገት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው በተጀመረው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ሕብረተሰቡን በንቃት በማሳተፍ ዘላቂ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በግብርና ምርት እድገታችን ውስጥ አንዱ ተስፋ የሰነቀው ጉዞ የሀገሪቱን ምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሰፊ መሰረት የጣለና ያገዘ መሆኑ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ፤ አማራ፣ ደቡብ፣ ትግራይ፣ ሶማሌና አፋር ክልሎች በሚገኙና በምግብ እጥረት በተጎዱ 12 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ ከ2010 ጀምሮ ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡

 

ለፕሮጀክቱ ማካሄጃ  ከተባበሩት መንግስታት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ፕሮግራም 11 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ መደረጉን ኃላፊው የገለፁ ሲሆን፤ ከሕዝብና ከመንግስት 144 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የቁሳቁስ፣ የጉልበትና የእውቀት ተሳትፎ እንደሚደረግ፤ እስከ 2014 የሚቆየው ፕሮጀክት ከ220 ሺህ በላይ ቤተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን፤ በዚህም የእንስሳት መኖ ልማት፣ ንብ ማነብ፣ በአፈርና ውሀ እቀባ፣ በደን ልማት፣ በአካባቢ ጥበቃና ተያያዥ መስኮች ከ140ሺህ በላይ ወጣቶችን ጨምሮ ሌሎችም የሕብረተሰብ  ክፍሎችን በማሳታፍ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ዶክተር ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብዝሐ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዮ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የብዝሐ ሕይወት ሀብቱ በሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ለማስቻል የተዘጋጀና ለብዝሐ ሕይወት ሀብት ልማት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ስራውን በሁሉም ወረዳዎች ለማስፋፋት  የደንና አካባቢ ሚኒስቴር፣  የብዝሐ ሕይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡

በሌላም በኩል ዘንድሮ የሚካሄደውን የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና እንክብካቤ ሥራ በተሻለ ውጤታማነት ለማስፈጸም ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የኦሮሚያ፤ ጋምቤላና ደቡብ ክልሎች መግለጻቸው ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው፡፡

የኦሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የተፋሰስ ልማትና የአፈርና ውሀ ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ ዘንድሮ የሚካሄደውን የተፋሰስ ልማት በክልሉ በተሻለ ሁኔታ ለማከናወን ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ ወደሥራ ከመገባቱ በፊት በየደረጃው ከሚገኙ የአመራር አካላትና ከሕዝቡ ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎአል፤ የክሂሎት ስልጠናም   ተሰጥቶአል፡፡ ባጠቃላይም በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃው ሥራ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕዝብ እንደሚሳተፍ ይገመታል፡፡

በዘመቻ መልክ ለአንድ ወር ከሚከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎች መካከል የተለያዩ የስነ አካላዊ፣ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ሥራዎች፣ 890 ሺህ ኪሎ ሜትር የእርከን ሥራ ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የውሀ ማስወገጃ እስትራክቸር፤ የእርጥበት ማቆያ፤ 514 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ውጭ ማድረግና ሌሎችም በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን ታቅዶአል፡፡

ከግብርና ልማቱ ጋር በተያያዘ የጋምቤላ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ተወካይ አቶ ኬት ቾል በክልሉ የዘንድሮውን የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ካለፉት ዓመታት በተሻለ ደረጃ ማከናወን እንዲቻል ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው በ2010 በጀት ዓመት 538 ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ አዳዲስ የሥነ-አካላዊ፣ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ሥራዎች ለማካሄድ እቅድ መያዙን በተያዘው ጥር ወር በአምስት ወረዳዎች የተለያዩ የሕዝብ አደረጃጀቶችን በመጠቀም የተፋሰስ ልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑ  ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ቦጋለ ሌንጮ በበኩላቸው የተፋሰስ ልማትን አስመልክቶ ለተሳታፊዎችና አመራር አካላት ቀደም ብሎ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸው በክልሉ በሚከናወነው የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራ በጉልበት የሚሳተፍ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሰው ኃይል  መለየቱን አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከናወኑ የአፈርና ውሀ እቀባ ሥራዎች ከጥቅም ውጪ ሆነው የነበሩ ተራሮች፣ የእርሻ፣ የደንና የግጦሽ መሬቶች አገግመው ወደ አገልግሎት ተመልሰዋል፡፡ የከርሰ ምድር ውሀ፤ የአፈር ለምነትና በመስኖ የሚለማው መሬት የጨመረ ሲሆን የአፈር መሸርሸር መጠንንም ዝቅ ለማድረግ ተችሎአል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በመኖ አቅርቦት፣ በማር ምርት መጨመር፣ በሴቶች ተጠቃሚነት፣ በድሕነት ቅነሳና በምግብ ዋስትና ላይ ጉልህ ድርሻ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን በመኽር እርሻ በ572ሺህ 200 ሔክታር ማሳ ላይ የለማ ሰብል በወቅቱ መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ የገለጸ ሲሆን በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ እያለ ዳኘ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በ2009/2010 የመኽር ወቅት በ640 ሺህ ሔክታር መሬት  ከለማው ሰብል 90 በመቶ የሚሆነውን በወቅቱ ለመሰብሰብ ተችሎአል፡፡

ሰብሉን በምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነርና የአርሶ አደሮችን የልማትና የአንድ ለአምስት አደረጃጀት በመጠቀም ለመሰብሰብ የተቻለ ሲሆን ከተሰበሰቡ የሰብል ምርቶች መካከል ጤፍ፤ ስንዴ፤ በቆሎ፤ ማሽላ፤ ገብስ፤ አተር፤ ባቄላ፤ ቦለቄና ሰሊጥ በብዛት ይገኙበታል፡፡ እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት የተገኘ ሲሆን ምርቱ ቀድሞ በተሰበሰበባቸውና ውሀገብ በሆኑ ማሳዎች ላይ የበጋ መስኖ ልማት ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ በመሰብሰብና በተደራጀ አግባብ መንቀሳቀሱ የምርት ብክነትን ለመቀነስ ያስቻለበት ሁኔታ ተፈጥሮአል፡፡ በዞኑ በመኽር ወቅት ከለማው ማሳ ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡