የሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ ልኡካን በክረምት ኦሎምፒክ ዝግጅት ዙሪያ ተወያዩ

የሰሜን ኮሪያ እና ደቡብ ኮሪያ ልኡካን በፒዮንግ ቻንግ የክረምት ኦሎምፒክ ዝግጅት ዙሪያ ለሁለተኛ ጊዜ ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡

ሁለቱ ኮሪያውያን ባሳለፍነው ሳምንት ተገናኝተው በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ላይ መምከራቸው ይታወቃል፡፡

በውይይታቸው በተለይ ደቡብ ኮሪያ የምታዘጋጀው የክረምት ኦሎምፒክ ትልቁ አጀንዳቸው ነበር፡፡

አሁን ደግሞ በርካታ የዓለማችን መገናኛ ብዙሃን ሁለቱ ሀገራት በኦሎምፒክ ጨዋታው አንድ እና የጋራ የሆነ የበረዶ ላይ ውድድር ወይም አይስ ሆኪ ቡድን ለመወከል ስለማሰባቸው እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡

ሀገራቱ ባለፈው ማክሰኞ ለምክክር ከተቀመጡ በኋላ ዳግም ሳምንት እንኳን ሳይሞላቸው በስድስተኛው ቀን ለሌላኛው ድርድር መቀመጣቸው ሁለቱ ሃገራት እርስ በእርስ ለመቀራረብ ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት የሚያሳይ ነውም እየተባለ ነው፡፡

በወታደር አልባዋ ታሪካዊት የገጠር መንደር ፓንሙንጆም መነጋገር የጀመሩት የሁለቱ ሀገራት ተወካዮች የሚወያዩበት አጀንዳ ምንም እንኳ በእርግጠኛነት ለማወቅ ቢስቸግርም ፒዮንግ ያንግ በፒዮንግ ቻንጉ የኦሎምፒክ መድረክ ላይ እንዴት ትሳተፍ የሚለው ርዕስ ሰፊውን ጊዜ የያዘ ነው፡፡

ከደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት እየተሰማ ባለው መረጃ ግን የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናትን የሚያሳትፈው እና ጠንከር ያሉ ውይይቶች የሚጠበቅበት ንግግር የፊታችን እሮብ የሚጠበቅ ነው፡፡

በዚህ ሳምንትም የሴዑል ልዑክ መሪ ሊ ው ሱንግ ከፒዮንግያንጉ አቻቸው ሁክ ቦንግ ጋር በፓንሙንጆም መታደማቸውም ታውቋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የደቡብ ኮሪያውን ፕሬዝዳንት ሙን ጄኢን አጎብዳጅ በሚል ወቅሰዋቸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የሁለቱን ሀገራት ባለስልጣናት ያገናኘው ውይይት ከሁለት ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው በመሆኑ የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማደስ ረገድ ያለው ፋይዳ የላቀ በመሆኑ ትልቅ ትርጉም ለማግኘትም ችሏል፡፡

ሰሜን ኮሪያ በኦሎምፒክ ኮሚቴዋ በኩል ብቁ አትሌቶቿን ለማስመዝገብ የመጨረሻው ቀን ካለፈ 4 ወራትን ቢያስቆጥርም የሀገራቱን የፖሊቲካ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባው ዓለማቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ለፒዮንግ ያንግ እድሉ አሁንም ክፍት ስለ መሆኑ በመግለጫው አረጋግጧል፡፡

ሁለቱ ኮሪያውያን ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በዓለማቀፍ የስፖርት ሁነት ላይ በአንድ ሰንደቅ አላማ ስር ሆነው ሲወዳደሩ ታይቶ አይታወቅም፡፡

ይሁን እንጂ ሁለቱ ሀገራት በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ስር ሆነው ደስታቸውን ሲገልጹ፤ የአንዱን ደስታ ሌላኛው ሲጋራ ግን በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡

ለዚህ ደግሞ በ2000 ዓ. ም የኦሎምፒክ ጨዋታውን ያዘጋጀችው የአውስትራሊያ ከተማ ሲድኒ በዋቢነት ትጠቀሳለች፡፡

የባለፈው ሳምንት የኮሪያውያኑ ንግግር ፒዮንግ ያንግ የኦሎምፒክ ልዑክ ለመላክ መዘጋጀት እዳለባት ከስምምነት ቢደርሱም ሀገራቱ ገና የሚነጋገሩበት በርካታ ነጥቦች እንዳሉዋቸው ግን ተነስቷል – ሲ ኤን ኤን ዘግቦታል