ዴሞክራሲ እንዲጠልቅ…

ኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የፍላጎት ጉዳይ ሳይሆን የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። መንግስት የአገራችንን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ስር እንዲሰድና በዚያው ልክም እንዲሰፋ ያደረጋቸውን ጥረቶች በርካታ ናቸው። ከህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ገዥው ፓርቲ አያደረገ ያለው የድርድር ሂደት የዚህ መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።

በድርድሮቹ እየታዩ ያሉት የመግባባት መንፈስ፣ ለአገር ጥቅም ሲባል የሚከናወኑ የሰጥቶ መቀበል አካሄዶች ዴሞክራሲ አገራችን ውስጥ ከተጨባጭ ሁኔታችን ጋር ስር እየሰደደና እየሰፋ መሆኑን ያሳያል። ድርድሮቹ ፋይዳቸው ዴሞክራሲን በማጥለቅ የተጀመረውን ምህዳር ይበልጥ ማጥለቅ ነው።

በህገ መንግስቱ ላይ የተደነገገውን የመደራጀት መብት ተከትሎ የየራሳቸው ደጋፊዎች ያሏቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመስርተውና በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መዝገብ ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተመስርተው ተግባራቸውን ሲወጡ ቆይተዋል። በተለይም የሽግግር መንግስቱን ተከትሎ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ዕውን ከሆነ በኋላ ለአምስት ዙሮች እስከተካሄዱት ምርጫዎች ድረስ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ያከበሩ ናቸው፤ የራሳቸው ችግሮች ቢኖርባቸውም።

ሆኖም የምርጫ ጉዳይ በመራጩ ህዝብ ፍላጎት በሚሰጥ ድምፅ ላይ የተመሰረተ እንጂ፣ በገዥው ፓርቲ አሊያም መንግስት በሚያደርጉት ችሮታ ላይ የሚከናወን ባለመሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በአብላጫ ድምፅ ተመራጭ ሊሆኑ አልቻሉም። በእኔ እምነት ሶስት ምክንያቶች ተቃዋሚዎቹ የህዝቡን አብላጫ ድምፅ እንዳያገኙ ምክንያት የሆኑ ይመስለኛል። አንደኛው፤ ተቃዋሚዎቹ በህገ መንግስቱና በህዝባቸው ከመተማመን ይልቅ በውጭ ኃይሎች የሚዘወር ዴሞክራሲን የሚሹ ሆነው መቅረባቸው ነው። 

ሁለተኛው፤ በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ሳቢያ በህዝቡ ውስጥ የተፈጠሩ ብሶቶችን ከማራገብና ቅንጭብጫቢ የኒየ-ሊበራሊዝን አስተሳሰብ ከማስተጋባት በስተቀር የህዝብን ቀልብና ልብ ሊገዙ የሚችሉ የነጠሩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ማቅረብ አለመቻላቸው ሲሆን፤ ሶስተኛው ደግሞ፤ ተቃዋሚዎቹ ራሳቸውን እንደ ፓርቲ ሲመሰርቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን እናጎለብታለን በሚል እሳቤ ይሁን እንጂ፣ ከአወቃቀራቸው ጀምሮ እርስ በርሳቸው የማይተማመኑና “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል ስሜታዊ ቁርኝት የተቧደኑ እንዲሁም በጥቅም ሽኩቻ ሳቢያ በምርጫ ሰሞን በአደባባይ ሲፈረካከሱና እርስ በርሳቸውም ሲወነጃጀሉ በመራጩ ህዝብ ዓይን ትዝብት ላይ ስለወደቁ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህ ሁኔታም ተቃዋሚዎቹ ፓርላማ ውስጥ ወንበር እንዳያገኙ እንዲሁም አሁን በሀገራችን ውስጥ የተፈጠረውንና በዓለማችን ላይ እንደ ጃፓን፣ ማሌዥያና ደቡብ አፍሪካ በመሳሰሉ ዴሞክራሲያዊ ሀገሮች ገቢራዊ እየሆነ የሚገኘው የአውራ ፓርቲ ፖለቲካዊ ስርዓት (Dominant Party Political System) ዕውን እንዲሆን ማድረጉ የሚካድ አይመስለኝም።

ይሁንና መንግስት በቅርቡ ‘ቁጥሩ ይነስ እንጂ ተቃዋሚዎችን የመረጠ የሀገራችን ህዝብ በመኖሩና የዚህ ህዝብ ድምፅ መሰማት ስላለበትም በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር አካሂዳለሁ’ ማለቱ አይዘነጋም። ለዚህም የምርጫ ህጉን ከማሻሻል ጀምሮ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ህገ መንግስቱን እስከማሻሻል ጭምር ድረስ በመሄድ የተዳቀለ የምርጫ ስርዓትን በመከተል የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድምፅ የሚሰማበትን ሁኔታ በመፍጠር የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ቃል ገብቷል። እርግጥ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከሚከተል እንዲሁም ዴሞክራሲን እንደ ሞትና ሽረት ጉዳይ አድርጎ ከሚመለከት ፓርቲና መንግስት የሚጠበቅ በመሆኑ፤ የተያዘው ቁርጠኝነት የሚያስመሰግንና “ይበል!” የሚያሰኝ ነው። ሊበረታታም ይገባል።

በአሁኑ ወቅት መንግስት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርጋቸው አበረታች ውይይቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ የተያዘው ቁርጠኝነት በሚፈለገው ፍጥነት መጎልበት ያለበት ይመስለኛል። ዴሞክራሲውን ለማስፋት በመንግስት በኩል የተያዘው ቁርጠኝነት ተጨባጭ መገለጫዎች ሊኖሩት ይገባል። ተቃዋሚዎችም ይህን ተስፋ በተሳሳተ መንገድ ተረድተው ወዳልተፈለገ እሰጥ አገባ ውስጥ እንዳይከታቸው ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ይመስለኛል።

እናም ከተቃዋሚዎቹ ጋር የሚካሄዱ ውይይቶችና ድርድሮች መነሻቸውና መድረሻቸው በግልፅ ተለይተው ሊገለፁና የጋራ ድምዳሜ ሊያዝባቸው ይገባል። ይህ ሲሆንም መንግስትና ገዥው ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጎልበት ያላቸውን ቁርጠኝነት ይበልጥ በመግለፅ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ የሚችሉ ይመስለኛል። አሊያ ግን በአሁኑ ወቅት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል የምንሰማቸው እንደ ‘ስልጣን እንጋራ’ ዓይነት የተሳሳሳቱ አስተሳሰቦችን በመፍጠር በአጠቃላይ ህዝቡ ውስጥ የማይገባ ምስል ሊያሲዙ ይችላሉ። በመሆኑም ለእኔ ከዚህ አኳያ ትክክለኛውን መንገድ ማሳየት ተገቢ ብቻ ሳይሆን፣ ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀቱን ለመጨመር በተያዘው ቁርጠኝነት ላይ አንድ ርምጃ መሄድ ጭምርም ነው።

በአንፃሩም ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረገው ውይይትና ድርድር፤ ፓርቲዎቹ ከመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታው ጋር ተያይዞ መንግስት ያለበትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ህፀፆቹን በግልፅ እንዲያይ ያደርጉታል። መንግስትም አግባብና ትክክለኛነት ያላቸውን አስተያየቶች በመቀበል ለስራው እንደ አንድ ድጋፍ እንዲጠቀምባቸው የመነሻ ሃሳቦች ሊሆኑት ይችላሉ።

ይህ ሁኔታም በአንድ በኩል ዴሞክራሲውን ለማስፋትና የህዝቦችን ተደማጭነት ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሰሚነት ድምፅ እንዲጨምር ዕድል ይሰጣል። በፓርላማ ደረጃ የሚኖረው የአሳታፊነት ዴሞክራሲም መንፈስና ተግባርም ይጎለብታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በአሁኑ ወቅት የአገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከማጎልበትና ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ነው።

በተለይ ከሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተጀመረው ድርድርና ክርክር ተጠቃሽ መሆኑን በማመላከት ሂደቱ በመቻቻል፣ በመደማመጥና ሰጥቶ በመቀበል መርህ ላይ በመመስረት ለመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መጠናከር የበኩሉን ሚና እያበረከተ ነው።

ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ ከተለያዩ ሲቪክ ማህበራት ጋር የተደረጉ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች ዴሞክራሲያዊ ባህልን ከማጎልበት አንጻር ጠቃሚ ሚና ተጫውቷል።

ሆኖም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የተደረጉ ውይይቶች የዴክራሲያዊ ስርዓቱ ለማጠናከር ከፍተኛ ስላለው ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።  በየደረጃው ያሉ የህዝብ ምክር ቤቶችና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት ለማጠናከር የተደረጉ ጥረቶችም ጎልብተው መቀጠል ይኖርባቸዋል። እንዳልኩት እዚህ አገር ውስጥ ያለው ሁኔታ ሰጥቶ የመቀበልና አሳታፊ የዴሞክራሲ ባህልን የሚያጎለብት በመሆኑ አሁንም ዴሞክራሲውን ለማጥለቅ ሁሉም በየፊናው የድርሻውን ማበርከት አለበት።