“ዴሞክራሲን ከማግኘት ይልቅ፤ ጠብቆ ማቆየቱ ይከብዳል”

የአንድ ብሔር ወይም ድርጅት የበላይነት የሚንጸባረቅበት አስተዳደር የሚፈጠረው፤ የህዝብን  ሳይሆን የቡድኖችን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚደረግ ጥረት መሆኑን መተማመን ይኖርብናል፡፡ ጉዳዩን ሳይንሳዊ በሆነ ጎዳና መመርመር እንችላለን፡፡ ሳይንስ አንድን ጉዳይ ሲያጠና፤  የሚጠናውን ነገር ወደ መጨረሻው ዝቅተኛ ክፍልፋይ አውርዶ የነገሩን መሠረታዊ ውቅር ለመለየት ይሞክራል፡፡ ስለዚህ አንድን ነገር በሳይንሳዊ መንገድ ለመረዳት የሚሞክር ማናቸውም አጥኚ፤ የነገሩን ዝቅተኛ አዋቃሪ ክፍል ለማግኘት ይሞክራል፡፡ ትልቁን ነገር ሸንሽኖ መሠረታዊ አዋቃሪ ክፍሉን ይመረምራል፡፡ በተፈጥሮም ሆነ በማህበራዊ ሳይንስ የጥናት ዘርፎች እንዲሁ ይደረጋል፡፡

አሁን የምንነጋገረው ስለማህበረሰብ ነው፡፡ ሳይንሳዊ የጥናት ዘዴን በተከተለ አካሄድ ማህበረሰብን ስንመረምረው፤ የአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ የመጨረሻ አዋቃሪ ቅንጣት ሴት እና ወንዶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱ በሌሉበት ማህበረሰብ አይኖርም፡፡ ስለማህበረሰብ መነጋገር አይቻልም፡፡ ከነዚህ ከሁለቱ (አንድ ሴት እና አንድ ወንድ) ማህበራዊ ትስስር ቤተሰብ ይገኛል፡፡ ቤተሰብ በመንደር ይኖራል፡፡ መንደር የዝቅተኛው ማህበረሰብ ጡብ ይሆናል፡፡ ብዙ መንደሮች ቀበሌ ይሆናሉ፡፡ እንዲህ – እንዲህ እያልን ሐገረ – መንግስት ከሚባል ሁሉን አካታች ማህበረሰብ እንደርሳለን፡፡

ታዲያ በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ የአንድ ግለሰብ፣ ቤተሰብ ወይም ቡድን የበላይነት ሲንጸባረቅ፤ የማህበረሰቡ ህይወት የተባላሸ ይሆናል፡፡ አንድ የመንደር አለቃ፣ የቀበሌ ሹም ሆነ የሐገር አስተዳዳሪ ሥልጣኑ በህዝብ ፈቃድ ያልተባረከ ሲሆን ወይም የሁሉንም አባላቱን የጋራ ጥቅም በእኩልነት ለማስከበር በሚያስችል መርህ ተወስኖ ለማስተዳደር ካልቻለ፤ ችግር ይፈጠራል፡፡ በመሆኑም፤ የብዙሃኑን ፍላጎት በማክበር፤ የመላውን ህዝብ ጥቅም የሚያስከብር ዓላማ ይዞ ያልተነሳ መንግስት ጸንቶ ሊቆም አይችልም፡፡

አንድን ህዝብ ከሌላው ለይቶ ለመጥቀም የሚሞክር መንግስት፤ በተጨባጭ በስልጣን ላይ ያለውን ቡድን ከመጥቀም አልፎ፤ እወክለዋለሁ ብሎ የሚያስበውን ህዝብ ጥቅም እንኳን ሊያስጠብቅ አይችልም፡፡ ሁለት ህዝቦችን እኩል ለማየት የማይችል መንግስት፤ በራሱ ውስጥ ያሉ ሁለት ዞኖችን፣ ወረዳዎችን፤ ክፍለ ከተሞችን፣ መንደሮችን፣ ቡድኖችን፣ ቤተሰቦችን እና ግለሰቦችን እኩል ለማየት አይችልም፡፡ ይህ መንግስት በፍትሕ እና በእኩልነት መርህ ላይ የቆመ ባለመሆኑ፤ እወክለዋለሁ ወይም እጠቅመዋለሁ እያለ ስሙን የሚጠራውን ህዝብ መነገጃ ያደርገው ይሆናል እንጂ የማህበረሰቡ አባላትን ጥቅም ሊያረጋግጥ አይችልም፡፡ ዛሬ ባይሆን ነገ፤ እዚህ ባይሆን እዚያ፤ ውሎ አድሮ እወክለዋለሁ የሚለው ህዝብ ተጻራሪ ኃይል መሆኑ አይቀርም፡፡

በሌላ በኩል፤ ሁሉንም ማህበረሰብ በፍትሕ እና በእኩልነት መርህ ለመምራት የሚጣጣር መንግስት ከሆነ፤ ይህ መንግስት በቋንቋም ሆነ በባህል ለማይመስሉት፤ በአጭሩ ለሰው ልጆች ሁሉ ሊጠቅም የሚችል መንግስት ይሆናል፡፡ በመሆኑም፤ የራሱን ብሔር ወይም ቡድን ጥቅም ለማስከበር የሚችል መንግስት፤ የሰው ልጆችን ሁሉ ጥቅም ለማስከበር በሚችል መርህ የሚመራ መንግስት ነው፡፡ ዣን ፖል ሳርትር፤ ‹‹አንድ ሰው ለራሱ ሲመርጥ ለሰው ልጆች ሁሉ ይመርጣል›› ይላል፡፡

የአብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ፍላጎት የማይከተልና በዴሞክራሲያዊ መርሆች የማይመራ መንግስት፤ ውሎ አድሮ በስሙ በሚነግድበት ህዝብ መካከል በሚኖሩ ልዩነቶች እየተሳበ ሚዛን የሚስት እና ከአንዱ ወይም ከሌላኛው ንዑስ ቡድን ጋር በመወገን፤ በመደብ፣ በቋንቋ፣ በብሔር ወይም በሌሎች ልዩነቶች ተጠልፎ የአንድ ቡድን አገልጋይ መሆኑ አይቀርም፡፡ ራሱን ከዚህ አይነት መሰናክል ለማዳን የሚያስችል የስነ ልቦና ወይም የመርህ ገደብ ሊኖረው ስለማይችል ሁሌም ሲሳሳት ይገኛል፡፡

ስለዚህ አንድ መንግስት እወክለዋለሁ የሚለውን ህዝብ ጭምር ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሊያገለግል የሚችለው፤ ሁሉንም በእኩልነት ለማገልገል የሚያስችል ወይም የሰው ልጆችን በመላ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል መርህ የሚከተል ከሆነ ብቻ ነው፡፡ በዚህ እይታ፤ አንድን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚችል መንግስት፤ ሁሉንም የሰው ልጆች ሁሉ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚችል መንግስት የመሆን ዕድል ይኖረዋል ማለት ይቻላል፡፡ አንድን ህዝብ ሊጠቅም የሚችል መንግስት፤ በመርህ የሚመራ እንጂ በአድሎ የሚሰራ መንግስት አይደለም፡፡ ለአንድ ቡድን ጠቃሚ ሆኖ የተገኘ ቡድን፤ ሁሉንም የፖለቲካ ማህበረሰብ አባላት ተጠቃሚ የሚያደርግ መንግስት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም፤ ሁሉንም የፖለቲካ ማህበረሰብ አባላት ተጠቃሚ በሚያደርግ መርህ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት፤ የአንድ የተወሰነ ህዝብ አገልጋይ ለመሆን አይችልም፡፡ እያንዳንዱ ብሔር-ብሔረሰብ እና ህዝብ በየራሱ ክልል፤ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ስርዓት በተዘረጋበት ሐገር፤ የአንድ ብሔር የበላይነት ሊፈጠር አይችልም፡፡

ሆኖም ቀደም ሲል እንደጠቀስነው፤ የብሔር – ብሔረሰብ ብዙነትን ለማክበር ታስቦ የተገነባው የፌደራል ስርዓታችን ወቅታዊ ተግዳሮት ሆኖ የወጣው ‹‹የአንድ ብሔር የበላይነት አለ›› የሚል አስተያየት ነው፡፡

ይህም የኢትዮጵያ ህዝቦችን ነባር የአብሮ መኖር ባህል እና የአንድነት ስሜት የሚጎዳ ክፉ እና አደገኛ አስተያየት ነው፡፡ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን የህወሐት ተላላኪ አድርጎ በማቅረብ እና የትግራይ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለየ ተጠቃሚ መሆኑን መግለጽ የተጀመረው ዛሬ አይደለም፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ደርዝ ይዞ የቆየ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ይህን አስተያየት ቀደም ሲል ጀምሮ አንዳንድ የግል ፕሬሶች፣ አንዳንድ የሐገር ውስጥ እና የውጭ ምሁራን፤ እንዲሁም የባህር ማዶ የዜና ተቋማት እና በቅርቡም የማህበራዊ ሚዲያ ተሳታፊዎች ያነሱታል፡፡ ይህን አስተያየት ያለ ጥያቄ ለመቀበል ዝግጁ የሆኑ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል፡፡ ይህ ክፉ አስተያየት በአንዳንድ የእህት ድርጅቶች አባላት ጭምር ሲንጸባረቅ መታየቱም የችግሩን አሳሳቢነት ያመለክታል፡፡

በዚህ መደናገር ውስጥ በአንድ ነገር እርግጠኛ መሆን ይገባናል፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለጸው፤ ‹‹የራሱን ብሔር ወይም ቡድን ጥቅም ለማስከበር የሚችል መንግስት፤ የሰው ልጆችን ሁሉ ጥቅም ለማስከበር በሚችል መርህ የሚመራ መንግስት ነው›› የሚለው ጉዳይ ሊሠመርበት ይገባል፡፡ ስለዚህ የአንድ ብሔር ወይም ቡድን ጥቅምን ለማስከበር የሚፈልግ ማናቸውም የፖለቲካዊ ኃይል፤ የሰው ልጆችን ሁሉ ጥቅም ለማስከበር በሚችል መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ መርህ ያፈነገጠ ኃይል፤ የተወሰኑ ሰዎችን ቡድናዊ ጥቅም ከማስከበር ተሻግሮ፤ ቆሜለታለሁ የሚለውን ህዝብ ጥቅም ሊያስከብር አይችልም፡፡ የህወሓትን የበላይነት በማረጋገጥ የትግራይ ህዝብን ጥቅም ማስከበር አይቻልም፡፡ ስለሆነም ‹‹የህወሓትን የበላይነት›› ቢኖር እንኳን፤ የተወሰኑ ሰዎች ጥቅም ሊከበር ካልሆነ፤ የትግራይ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደረግ ሁኔታ ሊፈጠር አይችልም፡፡

ሆኖም ‹‹የትግራይ ህዝብ የበላይነት አለ›› የሚል የተዛባ አመለካከት ተፈጥሯል፡፡ በዚህም ሳቢያ በተለያዩ የሐገሪቱ አካባቢዎች በላብ እና በወዛቸው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ለጭንቀት እና ለሥጋት ተዳርገዋል፡፡ አልፎ አልፎም አካላዊ ጥቃት እና የንብረት ውድመት ሲያስከትል አይተናል፡፡ ይህ የሐገሪቱን አንድነት እና የህዝቦችን ተከባብሮ የመኖር ነባር ባህል የሚሸረሽር አደገኛ እና የተዛባ አመለካከት በመሆኑ በፍጥነት መስተካከል ይገባዋል፡፡ ረጅም ርቀት ሊወስደን የሚችለውን ብሔራዊ አንድነታችንን በተዛባ አመለካከት እንዳናጠፋው መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡     

በረጅም ዘመናት የተገነባውን የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከጥቃት መጠበቅ ይገባናል፡፡ አንዳንድ ምሁራን፤ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ኢትዮጵያ በምትባለው ሐገር በሚኖሩ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ባህል ውስጥ የሚንጸባረቅ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህ ስሜት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ አዲሱ የፌደራል መንግስት፤ ይህን ስሜት በተሻለ መሠረት ላይ ለማቆም እና የተዛባ የታሪክ ቅርስን በማረም፤ ሐገሪቱ ህዝቦችዋን እንድትመስል ወይም የተስተካከለ ቁመና እንድትይዝ በማድረግ ጥረት የተመሠረተ ነው፡፡ አሁን የያዝነው አዲስ የሐገር ግንባታ ፕሮጀከት ከባህላዊ ወጥነት ይልቅ፤ ለባህላዊ ብዙነት ትኩረት የሚሰጥ ፕሮጀክት ነው፡፡ አሁን የያዝነው የብሔራዊ ስሜት ግንባታ፤ የባህል መመሳሰልን በመፍጠር ላይ የተመሠረተ ሳይሆን፤ የባህል ብዙነት በማክበር እና በማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በዚህ አውድ የአንድ ብሔር የበላይነት ሊፈጠር አይችልም፡፡

ታዲያ የሐገር ግንባታ ፕሮጀክታችን በመሠረቱ ከተለመደው የአስተሳሰብ ሞዴል የተለየ በመሆኑ አንዳንድ የውጭ ታዛቢዎች ጭምር የኢትዮጵያን የሐገር ግንባታ ጥረት እንደ ሙከራ ፕሮጀክት ይመለከቱታል፡፡ ይህ በአዲስ የአስተሳሰብ ሞዴል የሚከናወን የሐገር ግንባታ ፕሮጀክት ከነባሩ የተለየ በመሆኑ መደናገር መፍጠሩ፤ የሐሳብ ግብግብ ማስከተሉ፣ የሥነ ልቦና ቀውስ ማምጣቱ፣ አንዳንዶችንም በጥላቻ ለተበከለ የፖለቲካ ትግል ማሰለፉ አይቀርም፡፡ እንዲሁም ነባሩ እንዲጸና እና አዲሱ እንዲለመልም በሚፈልጉ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የሰላ ትግል መፍጠሩ ማድረጉ የማይቀር ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› በሥር ነቀል የለውጥ ሂደት ውስጥ አልፎ አዲስ ትርጉም ይዟል፡፡ የአዲሱ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› አስተሳሰብ፤ የሐገረ-ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን መጻዒ ዕድል መወሰን የሚችል ጥልቅ ተጽዕኖ ማሳረፉ በግልጽ ይታያል፡፡ ታዲያ የተጀመረው የአዲስ ሐገራዊ ስሜት ግንባታ ፕሮጀክት ስኬት የሚወሰነው፤ የአክራሪ ብሔርተኝነት ስሜት በሽታ ከተወገደ ነው፡፡

እንደሚታወቀው፤ ለኢትዩጵያ ብሔር-ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ሸክም እና ቀንበር ሆኖ የሚታየውና ባለፉት 40 ዓመታት ከተለያየ አካባቢ በተነሱ ቡድኖች ከባድ የፖለቲካ ተጋድሮት የገጠመው ‹‹የሄጅሞኒ ዶክትሪን›› ፈራርሷል፡፡ በቀጥታ የመገንጠል መብታቸው እንዲከበር ከሚጠይቁት ጀምሮ፤ በፖለቲካ መዋቅር ለውጥ ሊመለስ የሚችል ጥያቄ ያነሱ የፖለቲካ ቡድኖች የጠሉት የ‹‹ሄጅሞኒ ዶክትሪን›› ክስረት ገጥሞት ወድቋል፡፡ ጥያቄው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ ሊፈታ ባለመቻሉም፤ በተለያዩ ቡድኖች መካከል የተነሳው ግጭት ሐገሪቱን ከፖለቲካ ማጥ ውስጥ እንድትዘፈቅ አድርጓት ቆይቷል፡፡ እንደ ሐገር የመዝለቋን ጉዳይ አጠራጣሪ አድርጎት ታይቷል፡፡

ስለዚህ የሐገሪቱን አንድነት ለማዝለቅ፤ በአዲስ መዋቅር ላይ የተመሠረተ የሀገር ግንባታ ፕሮጀክት ተዘርግቷል፡፡ በዚህ ውስጥ የአክራሪ ብሔርተኝነት ስሜትም ሆነ ‹‹የጠቅላይ ግዛት›› አመለካከት አፍራሽ በመሆናቸው ልንታገላቸው ይገባል፡፡ የብሔር መሥመርን የተከተለ ፉክክር የብሔሮችን የመቻቻል ስሜት የሚጎዳ፤ በብሔሮች መካከል የጥላቻ ስሜት የሚፈጥር እና ግጭትን የሚቀሰቅስ አደገኛ ጎዳና ነው፡፡ ቁሳዊ ሐብትን ለመቆጣጠር በብሔረሰብ ቡድኖች መካከል የሚደረግ ሽሚያ የስርዓት ቀውስ ሊያስከትል የሚችል ችግር ነው፡፡ ስለዚህ ይህን መሰል ችግር ውስጥ እንዳንገባ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡

 

ግጭት እና ቁጣን ማስወገድ የሚቻለው፤ ግጭት ቀስቃሽ ነገሮችን በአግባቡ እየለዩ በማስወገድ ወይም በመቀነስ ነው፡፡ የሰዎችን አስተሳሰብ በመቀየር፣ ትብብርን በማበረታታት፣ ለህዝብ የሚቀርቡ የሁኔታ ትንታኔዎች በጥንቃቄ እንዲካሄዱ በማበረታታት እና ራስን ከሌሎች ጋር አንድ ለሚያደርጉ ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት ነው፡፡ በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት ያላቸውን መፍትሔዎች ለማስቀመጥ ጥረት በማድረግ እና ለጋራ ዓላማ ተባብሮ በመስራት ነው፡፡ እንደሚታወቀው፤ የፌደራል ሥርዓቱን ያጸናው ህገ መንግስት ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ በማድረግ ረገድ እንዳንድ ውስንቶች ያሉ ቢሆንም፤ በሌላ በምንም አግባብ ሊፈጸም በማይችል አኳኋን ብዙነት በማስተናገድ ረገድ ትልቅ ስኬት አቀዳጅቶናል፡፡

 

በመሆኑም፤ የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት፤ ቢያንስ አራት ጉልህ ጠቀሜታን አስገኝቷል ማለት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው፤ ሐገሪቱን ለከፍተኛ ጉዳት የዳረገውን ለአስርት ዓመታት የዘለቀ ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነትን ማስወገድ እና የብሔሮችን ግንኙነት ማሻሻል ብቻ ሳይሆን ከደርግ ውድቀት በኋላ ያንዛዣበበውን የመበታተን አደጋ እንዲገታ ማድረግ ችሏል፡፡ ጠብመንጃ ያነሱ ኃይሎች መሣሪያ ለማስቀመጥ ፈቃደኛ እንዲሆኑ አና በአዲሱ የፖለቲካ ስርዓት ተሳታፊ ለመሆን እንዲነሳሱ አድርጓል፡፡ በዚህም እንደ ዘመነ ደርግ እንደታየው፤ አገር አቀፍ የእርስ በእርስ ጦርነት የመነሳት ዕድሉን አስወግዶታል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ሂደት ሰፊው የሐገሪቱ ህዝብ ሰላም እና መረጋጋት ለማግኘት ችሏል፡፡

 

ሁለተኛ፤ የኢትዮጵያን የብሔር-ብሔረሰብ ብዙነት ከልብ መቀበሉ፤ የብሔር-ብሔረሰቦችን የመከባበር እና የመደጋገፍ ስሜት ለማዳበር የሚያስችል መደላድል ፈጥሯል፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች፤ የኢህአዴግ መንግስት የብሔር ቡድኖች ከየራሳቸው የማንነት ክበብ ተሻግረው ወይም የየራሳቸውን ማንነት እንደጠበቁ ከሌሎች የሐገሪቱ ብሔሮች ጋር አብሮ ለመኖር የሚያስችላቸውን የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ለአደጋ የሚያጋላጥ አካሄድ ይዟል በሚል የሚወቅሱ ምሁራን አሉ፡፡ ገዢው ፓርቲም በዚህ ረገድ ችግር መኖሩን ተቀብሏል፡፡ ነገር ግን አስተማማኝ ህብረት ለመፍጠር የሚያስችል መደላድል መኖሩ ሊካድ አይችልም፡፡

 

ለዘመናት የቆየው ሌሎችን የመጫን፣ የባህል እና የማንነት መዋጥን፣ ማዕከላዊነትን የሚያጠናክር ሁኔታ እንዲፈራርስ አድርጓል፡፡ የአናሳዎችን ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክን የማናናቅ እና ብሔር-ብሔረሰቦችን ክብር እና ማዕረግ የሚጎዳበት ሁኔታ እንዲለወጥ አድርጓል፡፡ ከሁሉም በላይ ያልተመጣጠነ የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ልማት እና በሐገሪቱ የሚገኙ በርካታ አናሳ ብሔረሰቦች የሚገለሉበትን ሁኔታ አስወግዷል፡፡ ለዘመናት የተገፉ አናሳዎችን እኩልነት በማረጋገጥ፤ አናሳዎች ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ የፖለቲካዊ እና ተቋማዊ እውቅና የሚያገኙበት ሁኔታን ፈጥሯል፡፡

 

ሦስተኛ፤ አናሳዎች በፖለቲካዊ መዋቅሩ የተሻለ ውክልና ማግኘት ችለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ የፖለቲካ ሂደቱ ውክልና ማግኘት ችለዋል፡፡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሀገሪቱ ቋንቋ፣ የሐይማኖት እና የባህል ቡድኖች ወኪል የሚሆኗቸውን ሰዎች በሁሉም መቋቅሮች ለማየት የተቻለበት ዘመን ሆኗል፡፡ የተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ሐገሪቱን መምሰል ችሏል፡፡ በዚህ ሂደት፤ የተወሰኑ ቡድኖች የበላይነት አለ የሚል ሐሳብ መነሳቱ ባይቅርም፤ በሐገሪቱ ታሪክ ወደር የለሽ በሆነ መጠን፤ በሥራ አስፈጻሚው አካል ሙሉ ቁመና የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህሎች እና ሐይማኖቶች ቀለሞች በግልጽ የሚታይበት ሆኗል፡፡ የፌዴራሉ መንግስት ተቋማት እና የፐብሊክ ሰርቪሱ በየጊዜው እያደገ በሚሄድ መጠን ብዙነታችን የሚንጸባረቅበት ሁኔታ ታይቷል፡፡

 

ሁሉንም አናሳዎች ባይሆን በሚበዙቱ ዘንድ የብሔራዊ ፕሮጀክቱ አካል የመሆን ስሜት እንዲፈጠር እና የመካተት አመለካከት እንዲፈጠር ያደረገው ይህ ስርዓት፤ ብዙዎችን የእኩል ተጋሪነት እና የእኩልነት መብት እንዲጎናጸፉ ያደረገው ይህ ስርዓት፤ ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን የኢትዮጵያ ሙሉ ዜጋ አድርጎ የማየት ዕድል የፈጠረላቸው ይህ ስርዓት፤ የሐገሪቱን ብሔር-ብሔረሰቦች የእርስ በእርስ ግንኙነት በእጅጉ እንዲሻሻለ እና አንዱ ለሌላው እውቅና የመስጠት አመለካከት እንዲዳብር ያደረገው ይህ ህገ መንግስታዊ ስርዓት፤ የራስን አካባቢ በራስ ማስተዳደር የሚያስችል ማዕቀፍ በመፍጠር አናሳዎች ፖለቲካዊ ሥልጣን እንዲይዙ አድርጓል፡፡ በታሪክ ዘመናት የተጣቃሚነት ዕድል ያልነበራቸው አናሳዎች፤ ሚዛናዊ የሐብት እኩል ተጠቃሚነት ዕድል እንዲያገኙ እና የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው እንዲጠናከር አድርጓል፡፡

 

አዲሱ ህግ መንግስታዊ ስርዓት የህዝቡን ሁለንተናዊ ህይወት ምን ያህል እንደ ቀየረው በግልጽ ለመገንዘብ የዳር ሐገር ህዝቦችን ህይወት መመለከት በቂ ነው፡፡ ጋምቤላን ቤኒሻንጉልን፣ አፋር እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተጨባጭ ሁኔታ ምስክር ነው፡፡

በመጨረሻም የፌደራላዊ ስርኣቱ፤ የመሐል ሐገር ህዝቦች ብቻ ሳይሆኑ፤ የዳር አገር ህዝቦችም በዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ እና ከሐገሪቱ ልማት ፍትሐዊ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችላቸውን አስተዳደር ተፈጥሯል፡፡ በማህበራዊ መስክ በትምህርት እና በጤና ረገድ የተፈጠረው ለውጥ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቂ ይሆናል፡፡  የአናሳ ብሔረሰቦች ቋንቋ በተለይ በአንደኛ ደረጃ የትምህርት መስጫ ቋንቋ ለመሆን በቅቷል፡፡ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በቤኒሻንጉል፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰብ፣ እና በኦሮሚያ ክልሎች የአርብቶ አደር አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ እና የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የአርብቶ አደር ልጆች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የትምህርት ዕድል አግኝተዋል፡፡ ክልላዊ የትምህርት ሚዲያዎች የሚስፋፉበት ዕቅድ ተነድፏል፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ አጓጊ የዕድገት ጎዳና ውስጥ መሆኗ ግልጽ ነው፡፡ ይህን በሚሊኒየም አንድ ጊዜ የሚገኝ በጎ ዕድል እንዳይደናቀፍ ነቅተን እንጠብቀው፡፡  ጥሩ ዕድሎችን ከመፍጠር ይልቅ፤ ጠብቆ ማዝለቁ ይበልጥ ፈታኝ መሆኑን ተገንዝበን፤ ለሥራ እንነሳ፡፡