ቱርክ ጦሯን ወደ ሰሜን ሶሪያዋ አፍሪን ግዛት ማንቀሳቀስ ጀመረች

ቱርክ የአየር እና የመሬት ሀይል ጦሯን ወደ ሰሜን ሶሪያ አፍሪን ግዛት ማንቀሳቀስ መጀመሯን ፕሬዝዳንት ረሲቭ ጣይብ ኤርዶሃን አስታወቁ፡፡

በሶሪያ ሰሜናዊ እና ቱርክ ደቡባዊ ድንበር ላይ የምትገኘው የአፍሪን ግዛት በአረብ ኩርዶች እና በሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች አብዛኛውን ቁጥር ይዘውት በሚገኙ ኩርዶች ቁጥጥር ስር ያለች ግዛት ናት፡፡

የአፍሪን ግዛትን ኩርዶች በአሜሪካ በመደገፍ ከሽብር ቡድኑ አይ ኤስ ነፃ ማውጣታቸውም  ይነገራል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች የሚገኙ ኩርዶች አሁን ላይ በግዛቷ ፒኬኬ ከተባለ የሽብር ቡድን ጋር በመተባበር በአካባቢው  ተጨማሪ ግዛት ሊመሰርቱ ይችላሉ በመባሉ ከጅምሩ ለመደምሰስ የቱርክ ወታደራዊ ኃይል ወደዚች ቦታ ጦሩን ማንቀሳቀሱን ነው ፕሬዝዳንት ረሲቭ ጣይብ ኤርዶሀን የገለፁት፡፡

ቱርክ በአፍሪን ግዛት ያንቀሳቀሰችው  ጦር ከኩርድ ታጣቂዎች ጋር በመፋለም በቦታው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን ለመፍጠር ሲባል እንደሆነም  ነው  የተነገረው፡፡

የኩርድ ታጣቂ ኃይሎች ግን ቱርክ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ነው ጦሯን ድንበር አስጥሳ ያስገባችው ሲሉ ይከሳሉ፡፡

የቱርክ ተዋጊ ጀቶች እና ቦምብ የተሸከሙ  አውሮፕላኖችም ከፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶሀን የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈፀም ወደ ሰሜናዊ የሶሪያ ግዛት አፍሪን መንቀሳቀሳቸው በኩርድ ኃይሎች ላይ ከፍተኛ ፍራቻን ዘርቷል ነው የተባለው፡፡

ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን አክለውም  አሁን የከፈቱት የአፍሪን ግዛትን የመቆጣጠር ዘመቻ የተጀመረው  በአሜሪካ በሚደገፉት በሶሪያ ኩርዶች እና አብረዋቸው  ከሚገኙት ቱርክ ሽብርተኛ ካለቻቸው  ፒኬኬ ቡድን ጋር በመሆን ከቱርክ ጋር ለአስርት አመታት ያክል ሲዋጉ እንደቆዩ አስታውሰዋል፡፡

አሜሪካ ቀደም ሲል ያስታጠቀቻቸው  የሶሪያ ኩርዶች የሽብር ቡድኑን አይኤስ አይ ኤስ በመዋጋት እና ይዟቸው የነበሩ ግዛቶችን መልሶ በመቆጣጠር ትልቅ ስም ያላቸው  ናቸው፡፡

ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን ግን በሶሪያ ለሚገኙት ለነዚህ ኃይሎች ጥሩ ስም አልሰጧቸውም፡፡

እርሳቸው  እንደሚሉት ሁሉም  የኩርድ ታጣቂ ኃይሎች ስማቸው ይቀያየር እንጂ አንድ አይነት ናቸው ፣ይሁን እና የማንቀይረው ሀቅም  እነዚህ ኃይሎች የሽብር ቡድን መሆናቸውን ነው  ብለዋል፡፡

አሁን ላይ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ደግሞ ከ8ሺህ እስከ 10ሺህ የሚደርሱ የኩርድ ታጣቂዎች በአፍሪን ግዛት ይገኛሉ፡፡

እንደዚህ መሆኑ ደግሞ  ቱርክ በቦታው  የሰፈነውና  የሽብር ቡድን ያለችው  ወደ እርሷ ግዛት እንዳይዘልቅ ለማጥፋት እና አካባቢውን ከእነዚህ ኃይሎች ለማፅዳት ጦሯን አንቀሳቅሳለች፡፡

የቱርክ ወታደራዊ ኃይል ግን በአፍሪን ግዛት ጥቃቱ ኢላማ የሚያደርገው  አሸባሪዎችን እንጂ  ሰላማዊ ዜጎችን እንደማይጨምር ነው  ያስታወቀው፡፡

ከቱርክ ወታደራዊ ኃይል ባለፈ  በሶሪያ ምድር ቱርክ ሽብርተኛ ያለቻቸውን የኩርድ ቡድኖችን ለመደምሰስ አሜሪካ እና ኔቶም አብረው እንደተሰለፉ ነው  የተነገረው፡፡

እስከ ቅርብ ድረስ የሶሪያ ኩርድ ታጣቂወችን ለመደምሰስ ሙሉ ዝግጅት ስታደርግ የቆየችው  አንካራ ከአፍሪን ግዛት ሙሉ በሙሉ ሽብርተኝነትን እንደምታጠፋ የቱርክ መከላከያ ሚኒስትሩ ኑሪቲን ካኒኪሊ አስታውቀዋል፡፡  

ከ2015 ጀምሮ በሶሪያ ወታደራዊ ዘመቻ በማካሄድ የበሽር አላሳድ መንግስትን ስትደግፍ የቆችው  ሞስኮም  አሁን ቱርክ በከፈተችው  የአፍሪን ዘመቻ አረንጓዴ መብራት እንዳበራችላት እና እንደምትደግፋት ነው የተነገረው፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግን ቱርክ በከፈተችው የአፍሪን ግዛት ዘመቻ ሽብርተኞች ላይ ብቻ ያነጣጠረ ዘመቻ እንዲሆንና ንፁሃን ዜጎች ግን እንዳይጎዱ አሳስቧል ሲል የዘገበው አልጀዚራ ነው፡፡