ዶክተር አብይ በዓለም መገናኛ ብዙሃን ዕይታ

ኢትዮጵያ ውስጥ የእርቅና የሰላም ድባብ ከረበበ ሁለት ወራት አለፉ። የምህረትና ይቅርታ አውድም እውን እየሆነ ነው። በተለያዩ ምክንያቶች የታሰሩ ግለሰቦችም እየተፈቱ ነው። ሰላማችንም ከጥቃቅን ጊዜያዊ ግጭቶች በስተቀር በአንፃራዊነት አስተማማኝ ሆኗል። በዚህም ሳቢያ፤ ሰላምን ለማምጣት ለስድስት ወራት ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሁለት ወሩ እንዲነሳ ተደርጓል። የፖለቲካው ምህዳር በመስፋቱም፤ በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር ፊት ለፊት በመወያየት በተለያዩ ህጎች ላይ ማሻሻያዎችን እያደረጉ ነው። እንዲሁም በውጭ ሀገር ሆነው ትጥቅ ትግል በማካሄድ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ተቃዋሚዎች፤ ጓዛቸውን ሸክፈው ወደ ሀገራቸው እየገቡ ነው። ይህ ፅሑፍ እስከተሰናዳበት ጊዜ ድረስ፤ በኦቦ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) እንዲሁም የኦነግ አመራር የነበሩት አቶ ዮናታን ዲቢሳ እና ኮሎኔል አበበ ገረሱ የትጥቅ ትግላቸውን እርግፍ አድርገው በመተው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል። በተመሳሳይ ሁኔታም በውጭ የሚገኙ ሌሎች ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅቶችም በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ወደ ሀገራቸው መግባታቸው የሚቀር አይመስለኝም። እናም በሀገሬ ውስጥ ገና ድርብ ድርብርብ ድሎችን ማየታችን አይቀሬ ነው።…  

የይቅርታ፣ የእቅርና የሰላም መሃንዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ ከሁለት ወራት ጥቂት እልፍ በሚል ጊዜ ውስጥ ብቻ ብዙ ለውጦችን ማምጣት ችለዋል። ዶክተር አብይ በሀገር ውስጥ ያካሄዷቸው ጉብኝቶች፤ በሀገሬ ህዝቦች መካከል ብሔራዊ መግባባትን ያጠናከሩ ብቻ አይደሉም—ከዚህ በተጨማሪም የነበረብንን የሰላም ስጋት በእጅጉ እንዲቀንስና ህዝቡም በሙሉ ልብ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ለማጠናከር ቀልቡን ወደ ልማት እንዲያዞር የተመቻቸ ሁኔታም የፈጠሩ እንጂ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ ሀገራት ያካሄዷቸው ጉብኝቶችም ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን ያስገኙልን ናቸው። ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራትም ይሁን ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር ያላትን የጋራ ተጠቃሚነት መርህን በፅኑ መሰረት ላይ መገንባት አስችለዋል—ጉብኝቶቹ። በተለያዩ ሀገራት ውስጥ በእስር ላይ የነበሩ ወገኖቻችንን በማስፈታትና ከእንግልት በመታደግ የኢትዮጵያዊነት መንፈስና ኩራት ከፍ እንዲል አድርገዋል። ጉብኝቶቹ ለኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስህቦችን ማምጣት የቻሉ እንዲሁም መልካም ጉብትናንና ከባቢያዊ ትስስሮችን ያጠናከሩ ናቸው። በዚህም ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የፈጠሩ ናቸው።

ከላይ የጠቀስኳቸውና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የከወኗቸው ተግባሮች፤ እዚህ ሀገር ውስጥ የምንኖርና እውነታውን የምናውቅ እንደ እኔ ዓይነት ዜጎች እማኝነታችንን የሰጠንበት ብቻ አይደለም። የተለያዩ ታላላቅ የዓለም መገናኛ ብዙሃን (Mainstream Media) ሳይቀሩ ምስክርነታቸውን የሰጡበት ሃቅ ነው። ታዲያ በዚህ ፅሑፌ ላይ፤ ከእነዚህ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ከቦታ ውስንነት አንፃር ጥቂቶቹን ብቻ ቀንጭቤ ላስቃኛችሁ እሞክራለሁ— “ኒውዮርክ ታይምስ”ን (New York Times)፣ ዘ ጋርዲያንን (The Guardian)፣ ኒውስ ዊክን (Newsweek)፣ የታዋቂዋ የቢቢሲ (BBC) ጋዜጠኛ ዜና በደዊ ዕይታን እንዲሁም የግብፅ ሚዲያዎችን አስደናቂ ምስክርነት።

“ኒውዮርክ ታይምስ” የተሰኘው ጋዜጣ በፖለቲካ አምዱ ስር ባሰፈረው ፅሑፍ፤ ዶክተር አብይን "በበሽታ፣ በረሃብ፣ በስደት፣ በጦርነትና በሙስና ለደቀቀችው አህጉር ስር ነቀል መፍትሔ ማምጣት የሚችል ባለ ብሩህ አዕምሮ ባለቤት" በማለት አድናቆቱን ችሯቸዋል። ይህ የጋዜጣው አባባል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገራችው ውስጥ የከወኗቸው ተግባሮች ለቀጣናው ብሎም ለአፍሪካ በአርአያነት ሊታይ የሚችል መሆኑን የሚያመላክት ነው።

ርግጥ በሽታ፣ ረሃብ፣ ስደትና ሙስና ባለባት አፍሪካ ውስጥ፤ እነዚህን ችግሮች በቅድሚያ ከሀገሩ፣ ቀጥሎም ከቀጣናው ጋር በጥምረት በመስራት እንዲሁም በአፍሪካ ደረጃ የአህጉሪቱን ችግሮች ለመቅረፍ ለለውጥ የሚያልም ብስለት ያለው ባለ ራዕይ መሪ ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ተፈጥሮ ባደላቸው ብሩህ አዕምሮ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በሀገራቸው ያመጡትን ለውጥ፤ በቀጣናው ብሎም በአፍሪካ ሊከውኑት እንደሚችሉ መናገር ይቻላል። ምክንያቱም በእኔ እምነት አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የአፍሪካን ችግር ለመቅረፍ ወሳኙ ጉዳይ፤ መፍትሔውን በማመንጨት ህዝቡን ወደ አንድነት በማምጣት ለለውጥ በቁርጠኝነት ሰርቶ የሚያሰራ መሪን የማግኘትና ያለማግኘት  ስለሆነ ነው። የጋዜጣው ዕይታ ይህን አፍሪካዊ ኑባሬ ያመላክታል ብዬ አስባለሁ።

“ዘ ጋርዲያን” የተሰኘው ጋዜጣም ዶክተር አብይን አስመልክቶ አቋሙን በሚያንፀባርቅበት በርዕሰ አንቀፁ ላይ እንዳተተው፤ "አፍሪካ ከማንዴላ ቀጥሎ ሀገሩንና ህዝቡን የሚወድ መሪ አገኘች" ብሏል። አዎ! ዶክተር አብይ ህዝባቸውንና ሀገራቸውን እንደሚወዱ በተግባር ያረጋገጡ መሪ ናቸው። በሀገር ውስጥ ህዝባቸው ከነበረበት የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንዲወጣ፤ የፍቅር፣ የእርቅና የሰላም ተግባሮችን በመፈፀም አንፃራዊ ሰላምን ማምጣት የቻሉ ህዝብ-ወዳጅ መሪ ናቸው። ባለፉት ጥቂት ወራቶች ውስጥ ብቻ ለህዝብ ያላቸውን ፍቅር ተግባር ገልፀዋል። በሀገር ውስጥ የህዝቡን ጥያቄዎች ሊመልሱ የሚችሉ ጉዳዩችን አንስተው ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት ተገቢውን ምላሽ ሰጥተዋል። ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ፤ የታመመን በመጠየቅና በማበረታታት ተግባራቸው ምን ያህል ለህብረተሰቡ ቅርብ እንደሆኑም በተግባር አስመስክረዋል።  

ለጉብኝት በሄዱባቸው ሀገራት ሁሉ፤ የዜጎችን ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት ከእስርና ከእንግልት የታደጉ ህዝብ አፍቃሪ መሪ ናቸው። በጂቡቲ፣ በሱዳን፣ በኬንያ፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ በኡጋንዳና በግብፅ ባካሄዷቸው ጉብኝቶች ዜጎችን አስፈትተዋል። ይዘዋቸው ከእርሳቸው ጋር ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ በማድረግም ህይወታቸውን በአዲስ ምዕራፍ እንዲመሩ ፈር አሲዘዋል። ይህም ዶክተር አብይ ለህዝባቸው ያላቸውን ፅኑ ፍቅር የሚያሳይ አንድ መገለጫ ይመስለኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሀገራቸው ነገ” ብሩህ ሆኖ እንዲነጋ ያላቸውን ፍላጎት እውን ለማድረግ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በሰላም ውስጥ በእኩል ተጠቃሚነት ተሳስሮ ለማደግ ሰፋፊ ስምምነቶችን አድርገዋል። ለሰላም ካላቸው ልባዊ ቁርጠኝነት ተነስተውም ላለፉት 18 ዓመታት በኢትዮ-ኤርትራ መካከል የነበረውን ‘ሞት አልባ ጦርነት’ እንዲያበቃ ረጅም ርቀት ተጉዘው የሰላም እጃቸውን ዘርግተዋል—ምንም እንኳን በኤርትራ በኩል እስካሁን ድረስ በይፋ የተሰጠ ምላሽ ባይኖርም። ያም ሆኖ፤ ዶክተር አብይ ይህን ሁሉ የከወኑትና የሚከውኑት ለህዝባቸውና ለሀገራቸው ካላቸው ፍቅር በመነጨ ነው። እናም በጋዜጣው “ከማንዴላ ቀጥሎ ህዝባቸውንና ሀገራቸውን የሚወዱ…” መባላቸው ቢያንሳቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይመስለኝም።     

ለዶክተር አብይ እማኝነቱን የሰጠው ሌላኛው ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን “ኒውስ ዊክ” የተሰኘው ታዋቂ መፅሔት ነው። መፅሔቱ ታላላቅ ጉዳዩችን በሚይዝበት በሽፋን ገፁ ላይ፤ "የሀገሩንና የአህጉሩን ችግሮች ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት በሚገባ ያስተዋለ ታላቅ መሪ” ሲል አሞካሽቷቸዋል። ትክክለኛና ተገቢ ዕይታ ነው።

‘የአንድን ችግር መፍትሔውን ማወቅ የችግሩን ግማሽ ያህል እንደመፍታት ይቆጠራል’ እንደሚባለው፤ ዶክተር አብይ ሀገራችን በሁከት በምትታመስበት ወቅት፤ መፍትሔውን ለማምጣት ምን ማድረግ እንደሚገባ ‘ከኦቦ ለማ መገርሳ ቲም’ ጋር ሆነው ሲናገሩ በተለያዩ ወቅቶች አድምጫለሁ። በህዝብ ትግል ወደ ስልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ‘ከእነ ኦቦ ለማ ቲም’ ጋር ሆነው ይሰጧቸው ከነበሩት መግለጫዎች በመነሳት፤ የዚህን ሀገር ችግር ፈውስ በእጃቸው ያስገቡ መሪዎች እንደነበሩ ብናገር ከእውነታው መራቅ አይሆንብኝም።

እናም ዶክተር አብይ ለኢትዮጵያችን ችግር መፍትሔ በማበጀት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አንፃራዊ ሰላምና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንድንሻገር ማድረጋቸው፤ ስልጣን ከመያዛቸው በፊትም የችግሩ እልባት በእጃቸው እንደነበር የሚያሳይ ሃቅ ይመስለኛል። ይህም የሰውዬውን ብስለትና የመፍትሔ አባትነት የሚያመላክት ከመሆኑም በላይ፤ ወደፊትም ለአህጉሪቱ መስራት የሚያስችላቸው እምቅ አቅም ባለቤት እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ነው ብዬ አስባለሁ። በመሆኑም መፅሔቱ ለእርሳቸው የሰጠው አድናቆት፤ ከሚያራምዱት የእርቅ፣ የፍቅር፣ የሰላምና የአንድነት ብሎም የአብሮነት አቋም ጠንካራ ስብዕናቸው ተቆርሶ የሚታይ ነው።

ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ምስክርነቱን የሰጠው ሌላኛው ዓለም አቀፍ ሚዲያ  “ቢቢሲ” ነው—በታዋቂ ጋዜጠኛው ዜና በደዊ “Hard talk” በተሰኘው ፕሮግራሙ ላይ። ጋዜጠኛዋ ጠቅላይ ሚኒስትሩን፤ “ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የማንሳት፣ ተቃዋሚዎች ከእስር በመፍታት እንደልባቸው እንዲንቀሳቀሱ የማድረግና እንዲሁም በሀገሪቱ በመንግስት ስር የነበሩ ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታነት የማዞር የመሳሰሉ ታላላቅ ለውጦችን ያደረጉ መሪ ናቸው” ስትል አድናቆቷን ቸራቸዋለች። የጋዜጠኛዋ አባባል፤ ቀደም ሲል በመግቢያዬ ላይ የገለፅኳቸውን አንፃራዊ ሰላምን የማጥጣት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት እንዲሀም ህዝቡ ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት በማተኮር ዕድገቱን እንዲያሳልጥ በዶክተር አብይ ተከናውነዋል ያልኳቸውን ጉዳዩች የሚያረጋግጥ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝቡ በተሻለ ህይወት ውስጥ እንዲያልፍና በሀገራችን እየተከናወነ ያለው የልማት ስራ ወደ ታች ወርዶ ‘የህብረተሰቡን ጉሮሮ ምን ያህል አርጥቧል?’ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በቅድሚያ ጋሬጣዎችን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ከድርጅታቸው ጋር የመከሩበት እውነታንም የሚገልፅ ነው—የጋዜጠኛ ዜና በደዊ ዕይታ። የሀገራችንን ዕድገት ከፍታ ለመጨመር ከፊት ለፊት የተደቀነውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትሩና ድርጅታቸው በመንግስት እጅ የነበሩት የልማት ድርጅቶች በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ይዞታ እንዲዞሩ መወሰናቸው፤ በዕድገቱ ላይ የሚታየውን ማነቆ በመፍታት ልማቱ አካታች የሆነ ህዝባዊ ተጠቃሚነትን እውን የሚያደርግ ነው። ይህም በቅርቡ ከጋና የተረከብነው የአፍሪካ ኢኮኖሚ መሪነታችን ሳይንገራገጭ ግለቱን ጠብቆ እንዲጓዝ የሚያደርግ አቅምን ይፈጥራል። የጋዜጠኛ ዜና በደዊ ተደማሪ ዕይታም ከዚህ አኳያ የሚታይ ነው።

የዚህን ፅሑፍ አቅራቢ እጅግ ያስደነቀኝ ሌላኛው ጉዳይ፤ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን ያልተለመደ የአዘጋገብ ሁኔታ ነው። ለወትሮው ‘አንዲትም የውሃ ጠብታ አትነካብንም’ ለማለት “blood is thicker than water” (ደም ከውሃ ይወፍራል) የሚለውን አባባል ገልብጠው “water is thicker than blood” (ውሃ ከደም ይወፍራል) የሚሉትና ሰርክ በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ዘገባዎችን የሚያቀርቡ አንዳንድ ግብፃዊያን ሚዲያዎች ሳይቀሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን አስመልክተው አንድ ዓይነት ቋንቋ ሲናገሩ አድምጫለሁ። በማሳመንና በማግባባት የሚዲያን ዕይታ የመቀየር ሌላኛው ዲፕሎማሲያዊ ድል።  

ሰሞኑን ወደ ግብፅ አቅንተው ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ጋር በህዳሴው ግድብና በሌሎች የሁለትዮሽ ሀገራዊ ጉዳዩች ዙሪያ ተነጋግረውና በተለያዩ ምክንያቶች ታስረው የነበሩ 32 ዜጎቻቸውን ከእስር አስፈትተው የተመለሱት ዶክተር አብይ በግብፃዊያኑ ሚዲያዎች “በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ለዘመናት የነበረውን ስጋትና ጥርጣሬ ያስወገደ ወጣት መሪ” የሚል አድናቆት ተሰጥቷቸዋል። በእኔ እምነት፤ ይህ የግብፅ ሚዲያዎች አዲስ ምልከታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን የማግባባትና የዲፕሎማሲ ክህሎት ጥንካሬን የሚያሳይ ነው። በእውነቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ አንድ ፅንፍ ብቻ ይዘው በመዘገብ የሚታወቁት የግብፅ ሚዲያዎች እንኳን ሳይቀሩ ለዶክተር አብይ እንዲህ ዓይነት እማኝነት መስጠታቸው ቀደም ሲል ሌሎች መገናኛ ብዙሃን የገለጿቸውን የሰውዬውን ትክክለኛ ማንነት የሚመሰክሩ ናቸው።

እናም ለእኔ ዶክተር አብይ ታላላቅ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን በአንድ ዓይነት አስተሳሰብና ቋንቋ ስለ እርሳቸው እንዲናገሩ ያደረጉ መሪ ናቸው። ለወትሮው ስለ አፍሪካና ህዝቦቿ ረሃብ፣ ቸነፈር፣ ስደትና ሞት ብቻ በመዘገብ የሚታወቁት መገናኛ ብዙሃኑ፤ ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሰጡት እማኝነት፤ የዶክተሩ ህዝብንና ሀገርን የመውደድ፣ በቀጣናው እያከናወኑ ያሉትን የመሪነት ሚና ብሎም የአፍሪካ መፍትሔ አመንጪነታቸውን በግልፅ ከመገንዘባቸው የመጣ ይመስለኛል። በመሆኑም እኔም እንደ ዜጋ በእነዚህ ተግባሮቻቸው ህዝባችንንና ሀገሬን ላኮሩ መሪያችን ረጅም ዕድሜን እየተመኘሁ፤ ሁሉም ዜጋ ከእርሳቸው ጎን በመቆምና በተለሙት ጎዳና አብሮ በመጓዝ፤ የፍቅርን፣ የእርቅን፣ የሰላምንና የአንድነት ኢትዮጵያዊ ብሎም አፍሪካዊ ፅዋን ከፍ አድርጎ ሊጎነጭ ይገባል እላለሁ።