ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ለኤርትራ መንግስት ልኡካን በብሄራዊ ቤተ መንግስት የእራት ግብዣ አደረጉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለኤርትራ መንግስት ልኡካን ቡድን በብሄራዊ ቤተ መንግስት የእራት ግብዣ አድርገዋል።

በእራት ግብዣው ወቅት ባደረጉት ንግግርም፥ “ዛሬ ልዩ ቀን ነው፤ በኤርትራውያን እና በኢትዮጵያውያን መካከል ብዙ ጉጉት አለ” ብለዋል።

“የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ከኤርትራ ወንድሞቻቸው ጋር አብረው ፈጣሪን ማመስገን ይፈልጋሉ፤ አትሌቶቻችን አስመራ እና ምፅዋ ላይ የመሮጥ ጉጉት አላቸው” ሲሉም ተናግረዋል።

አርቲስቶቻችንም ባለፉት ዓመታት በሰሯቸው ፊልሞች እና ሙዚቃዎች የሁለቱን ህዝቦች ወንድማማችነት ለማሳያት ሞክረዋል ሲሉም ገልፀዋል።

ከኤርትራ ወንድሞቻችን ጋር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ኑሮ፣ በባህል በርካታ የሚያስተሳስሩን ነገሮች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ “ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ፍቅር ተጠምተን ነበር” ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የፍቅር እና የሰላም ጥሪውን ተቀብለው እነዚህ ታላላቅ ሰዎችን በመላካቸው ምስጋና ይገባቸዋል ያሉ ሲሆን፥ ለዚህ ቀን እንኳን አበቃችሁ ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ በኩል እርስ በራሳቸን በውስጥ፤ እንዲሁም ከሁሉም ጎረቤቶች ጋር በተለይም ከኤርትራ ጋር ከፍተኛ እርቅ እና ሰላም የመፍጠር ፍላጎት አለ ሲሉም አብራርተዋል።

ምክንያቱም ጥላቻ እና ብሽሽቅ አሁን ባለንበት እድሜ የሚያዋጣ ስላልሆነ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ አሁን ባለንበት ወቅት ከኤርትራ ጋር ብሽሽቅ ሳይሆን ሰላም እና ፍቅር ነው የሚያስፈልገው ሲሉም አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዛሬው እለት አዲስ አበባ ለገባው የኤርትራ መንግሥት ከፋተኛ የልኡካን ቡድን ነው በብሄራዊ ቤተመንግስት የእራት ግብዣ ያደረጉት።

በእራት ግብዣው ላይም የፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ አማካሪና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የማነ ገብረአብ እና የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ኦስማን ሳለህን ጨምሮ የሀይማኖት አባቶች፣ አትሌቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ሌሎች ተገኝተዋል።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባሳለፍነው ሳምንት በድንበር ጉዳይ ላይ የሚነጋገር የሀገራቸውን ልዑክ ወደ አዲስ አበባ ለመላክ ማሰባቸውን መናገራቸው ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ ነው የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ገንቢ ውይይት የሚያደርግ ከፍተኛ ልዑኩን በዛሬው እለት ወደ አዲስ አበባ የላከው።

ልኡኩ በአዲስ አበባ ቆይታውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር የሚወያይ መሆኑንም ለማወቅ ችለናል።( ኤፍቢሲ)