የፖለቲካ ነጋዴዎች እጃችሁን ሰብስቡ

ዛሬ በሁለት አስርት ዓመታት የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ትግል፤ በንጽጽር ከተነሳነበት ሁኔታ እጅግ የተሻለ ደረጃ ላይ መድረሳችንን በማስታወስ የሕዝቡን ልብ ማሸነፍ አይቻልም፡፡ ይህን ጉዳይ ህዝቡ ከካድሬዎች ቃል በላይ እርሱ በኑሮው አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ ነገር ግን አሁን በኑሮው የሚገጥሙት ፈተናዎች እንዲወገዱለት ይፈልጋል፡፡ አሁን መሪው ድርጅት እና የሚመራው መንግስት የሚመዘኑት እነዚህን ፈተናዎች አርኪ በሆነ ደረጃ መመለስ በመቻላቸው እና ባለመቻላቸው ብቻ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ትግሉ ከትናንት ዛሬ ከባድ እየሆኑ መምጣቱን ያመለክታል፡፡ በዚሁ ልክ የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ወሳኝ የህልውና ጥያቄዎች የመሆናቸው ጉዳይ ተጠናክሮ ይወጣል፡፡

 

ዶ/ር አቢይ አህመድ እንደ ተናገሩት፤ የሐገራችን የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በስልጣን በመቆየት ሒሳብ የሚታዩ ጉዳዮች አይደሉም፡፡ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር እጅግ ውስብስብ ከሆነ እና ስር ከሰደደ ድህነት ለመውጣት የሚያስችሉን ወይም ምቹ የልማት ዕድል የሚጥሩልን መሣሪያዎች ናቸው፡፡ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር፤ የህዝቡ የወደፊት ዕድሉ ሁሉ ጨለማ መስሎ ታይቶት በተስፋ መቁረጥ ላይ የተመሠረተ ጎዳና እንዳይከተል እና ፋይዳ ወደ ሌለው ትርምስ እና ደም መፋሰስ እንዳንገባ የሚጠብቁን፤ ከሐገራዊ ህልውና ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ የግጭት እና የጦርነትን ፖለቲካዊ ምንጮች በማድረቅ ለልማት የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያግዙ፤ የልማት፣ የሰላም እና የሐገራዊ ህልውና ዋስትና የሆኑ ክቡር ግቦች ናቸው፡፡

 

የሀገር አንድነትን መጠናከርና መላላት (ከጠናም መፈራረስ) የሚወስኑ ወሳኝ የስበት ኃይሎች ናቸው፡፡ የፖለቲካ ጅኦግራፊ ምሁራን፤ የሀገር አንድነትን መጠናከርና መላላት ሁለት የስበት (centripetal forces) እና የግፊት ኃይሎች (centrifugal forces) መኖራቸውን ይናገራሉ። የስበት ኃይሎች የተባሉት የአንድን ሀገር ሕዝብ አንድነት የሚያጠናክሩ ልዩ ልዩ ኃይሎች ሲሆኑ፤ የግፊት ኃይሎች የተባሉት ደግሞ ለአንድ ሀገር ሕዝብ መበታተን እና ለሀገር መፍረስ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው።

 

የስበት ኃይሎች ከግፊት ኃይሎች የበለጠ ብርቱ ከሆኑ የሀገርና የሕዝብ አንድነት እየጠነከረ ይሄዳል። የግፊት ኃይሎች ከስበት ኃይሎች ይልቅ የሚጠነክሩ ከሆኑ ግን የሀገር እና የሕዝብ አንድነት እየላላ ይሄድና ሀገር እስከ መፍረስ ሕዝብም እስከ መበተን ሊደርስ ይችላል ይላሉ።

 

የፖለቲካ ጅኦግራፊ ምሁራን የሚጠቅሷቸው አራት ዋና ዋና የስበት ኃይሎች (centripetal forces)፤ የሐገር ፍቅር (nationalism)፤ ህብረት ፈጣሪ ተቋማት (unifying institutions ለምሳሌ፤ ትምህርት ቤቶች፤ የመከላከያ ሠራዊት ወዘተ)፤ ቀልጣፋ የመንግሥት አስተዳደር (effective government administration)፤ እና  የመጓጓዣ እና የመገናኛ  ስርዓት (systems of transportation and communication) ናቸው።

 

የኢትዮጵያ የሓገር ግንባታ ሂደት በሌሎች ሌሎች ሐገሮች ከተካሄደው የሐገር ግንባታ ሂደት ጋር ሲነጻጸር የረባ ልዩነት ባይኖረውም፤ በተጨባጭ ማህበራዊ እውነታዎች ሳቢያ አስቸጋሪ ገጽታዎች ሊይዝ የሚችለው የሐገር ግንባታ ሂደታችን፤ በተሟላ የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ስርዓት ግንባታ ውጭ ሊሳካ የሚችል አይደለም፡፡

 

የሐገራችን ህዝብ በእርስ በርስ ጦርነት፤ በስደት (በፍልሰት)፣ በጋብቻ፣ በንግድ፣ የውጭ ጠላትን አብሮ በመመከት፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው-ሰራሽ የሆኑ (ክፉ እና ደግ የሆኑ) ነገሮችን ለረዥም ጊዜ አብሮ በመካፈል እና በመሳሰሉት የተለያዩ ክስተቶች ውስጥ በማለፍ ጠንካራ ዝምድ እና ትስስር የፈጠረ ህዝብ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ወጣ ገባው የሐገራችን መልክዐ ምድር፤ ደካማው ኢኮኖሚ፣ የትራንስፖርት እና የኮምዩኒኬሽን መሠረተ ልማት የህዝቦችን ግንኙነት መገደቡ አልቀረም፡፡ የተጠናከረ የኢኮኖሚ ልማት እና የመሠረተ ልማት መስፋፋት ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ የአንዱ አካባቢ ተወላጅ ወደ ሌላው አካባቢ በቀላሉ መንቀሳቀስ ሕዝብ ከህዝብ ለማተዋወቅ የሚችልበት ሰፊ ዕድል ስለሚፈጠር የሐገርን አንድነት ስሜቱ ይበልጥ የሚጠናከርበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር፡፡

 

ታዲያ ከላይ የተዘረዘሩት የስበት ኃይሎች (centripetal forces) አንድነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉት በጸጥታው፤ በአገልግሎት አሰጣጡ፤ በሀብት ክፍፍሉ፤ በፍርድ እና ፍትሕ አሰጣጡ፤ በሕዝብ ተሳትፎ እና በሌሎች መስኮች ጭምር ሚዛናዊነቱ የተጠበቀ አሰራር እንዲሰፍን መንግሥት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ነው። ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር ወሳኝ የሐገር ግንባታ አጀንዳዎች የሚሆኑት በዚህ የተነሳ ነው፡፡

 

ከዚህ በተጨማሪ፤ የሐገርን ፍቅር ለማዳበር ትምህርት ቤቶች (በተለይም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች) ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። በሰንደቅ ዓላማ፤በመዝሙር፤ በዘፈን እና በመሳሰሉት ጉዳዮች አማካይነት፤ ከህጻንነት ጀምረን ዜጎች የሐገር ፍቅር በአእምሯቸው እንዲሰርጽ ማድረግም አስፈላጊ ነው፡፡

 

ኢትዮጵያውያን ለሐገራቸው ከፍተኛ ፍቅር ያላቸው መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ የሐገራቸውን ድንበር ለማስከበር እና ከጠላት ለመጠበቅ መስዋዕት ለመሆን ወትሮ ዝግጁዎች ናቸው፡፡ የጦርነት አዋጅ በታወጀ ቁጥር ሚስቴን ልጄን፤ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ በየጦር ሜዳው በመሰዋት ለሐገራቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር አስመስክረዋል።

ሆኖም ይህ ዓይነት ጠንካራ የሐገር ፍቅር ስሜት በኢትዮጵያ ምድር ሁሉ ወጥነት ነበረው ማለት አይቻልም። ወጥነት እንዳይኖረው የሚያደርጉ ከመንግሥት አቅም፣ ከመልክዐ ምድር እና ከብዝሐነት ጋር የተያያዙ በርካታ ምክንያቶች ነበሩ።  ሰፊ መሬት እና ብዙ ብሔር -ብሔረሰብ  በውስጧ ያካተተችውን ኢትዮጵያን በአሀዳዊ የመንግስት አስተዳደር ለመያዝ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ማስከተሉ አልቀረም፡፡

 

እንደሚታወቀው፤ የፖለቲካ ጆግራፊ ምሁራን የግፊት ኃይሎች (centrifugal forces) ብለው የሚጠሯቸው እና አንድነትን የሚፈታተኑ፤ የበታኝነት ሚና የሚጫወቱ፤ ለአሀዳዊ ሐገር ቀጣይነት መሰናክል ይሆናሉ በሚል ከሚጠቅሷቸው ነገሮች መካከል፤ የቋንቋዎች፣ የብሔሮች እና የሃይማኖቶች ብዛት፤ እንዲሁም ከብሔሮች፤ ከቋንቋዎች እና ከሃይማኖቶች ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የባህል ልዩነቶች ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ ስለዚህ ህዝቦችን አንድ ቋንቋ (አማርኛ) ተናጋሪ በማድረግ የሕዝቦችን አንድነት፤ የሐገርን ቀጣይነት ወይም የስበቱን ኃይል ያጠናክረዋል የሚለው አስተሳሰብ በሌሎች አካባቢዎች የሰራ ቢሆንም፤ በኢትዮጵያ ሊሰራ የሚችልበት ዕድል አልነበረውም፡፡ ይህን አስተሳሰብ የሚቀናቀን እና የሚገዳደር አስተሳሰብ ወይም ኃይል ሲነሳ፤ የሕዝቦችን አንድነት እና የሐገርን ቀጣይነት ማረጋገጥ የሚችል አልሆነም፡፡

 

ሐገራችን ከ80 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ በርካታ ብሔር-ብሔረሰቦች እና ሐይማኖቶች የሚገኙባት ሐገር በመሆኗ፤ ሊፈጠር የሚችለውን የስበትን (የአንድነትን) ኃይል የሚያላላ ራሱን የቻለ ተግዳሮት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የሐገር የአስተዳደር ብልሹነት እና የሕዝቦችን ግንኙነት ገድቦ የኖረው የመልክዐ ምድር ወጥ-ገባነት ሳይቀር የግፊት ግንኙነትን የማሰናከል ሚና ይጫወታሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ብዙ የግፊት ኃይሎች የሚፈታተኗት ሐገር ነች።

 

እነዚህ ብሔር-ብሔረሰቦች በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ በመኖራቸው ብቻ ኢትዮጵያዊያን መባላቸው ባይቀርም፤ በአስተዳደር ብልሹነት የተነሳ በሚደርስባቸው በደል፤ በኢኮኖሚ እና በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች አሰጣጥ የተረሱ እና ወደ ዳር የተገፉ በመሆናቸው መከፋታቸው አይቀርም፡፡ በኢትዮጵያ ዓይነተኛ የሚባለው የግፊት ኃይል ብሔር-ብሔረሰቦች እና የቋንቋዎች ብዛት መሆኑ ባይካድም፤ የአስተዳደር ብልሹነትም ቀላል ሚና ያለው አይደለም፡፡ የአስተዳደር ብልሹነት ከፍ ሲል የጠቀስናቸውን የስበት ኃይሎች ጭምር የሚያኮላሽ አደገኛ የግፊት (በታኝ) ኃይል ነው።

 

በዚህ ሁኔታ ስር የሰደደ የሐገር ፍቅር ሊፈጠር አይችልም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ የምትባል ሐገር ኖረች – አልኖረች ደንታ የማይሰጣቸው እና ራሳችን እንችላለን (እንገነጠላለን) የሚሉ ኃይሎች ይነሳሉ፡፡ ግፊት ሰጪ (በታኝ) ኃይሎች ይጠናከራሉ። ሐገራችን የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ልዩ ልዩ ብሔር-ብሔረሰቦች ያሏት በመሆኗ፤ ለቡድን መብት እውቅና መስጠት ብቻ ሳይሆን በጣም አስተዋይ፤ ሚዛናዊ እና አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ካልሰፈነ በስተቀር፤ ህልውናዋ አደጋ ይጋረጥበታል፡፡ በአጭሩ ኢትዮጵያ ለመፈረካከስ እና ለመፍረስ የሚያስችል ጠንካራ እና በርካታ የግፊት ኃይል ያለባት ሐገር በመሆኗ፤ ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ይሆናል፡፡

  

መንግስት፤ ‹‹የዴሞክራሲ እና የመልካም ስርዓት መገንባት ከተሳነን እጅግ ዘግናኝ በሆነ እልቂት ተንጠን ረጅም ባልሆነ ጊዜ ውስጥ እንበታተናለን›› የሚለው ለዚህ ነው፡፡ ኢህአዴግ፤ ‹‹ህልውናችንን ለማረጋገጥ ከዴሞክራሲ እና ከመልካም አስተዳደር ግንባታ ውጪ አማራጭ የለንም፡፡ በዚህ ዓላማ ላይ መንሸራተትን፣ ወደ ኋላ መመለስን፣ ሽንፈትን መቀበል አይቻልም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሽንፈት ማለት እንኳንስ ለመሸከም ለማሰብም የሚከብድ ጥፋት የሚያስከትል ነገር ይሆናል›› የሚለው ችግሩን በውል በመገንዘቡ ነው፡፡

 

የቡድን መብት የተከበረው፤ ሕዝቦች በየራሳቸው የጎሳ ጐጆዎች ተኮድኩደው እንዲቀመጡ፤ ወደ ሌላ ክልል ሲሄዱ በባዕድ ሐገር የሚኖሩ ያህል እንዲሳቀቁ፤ አለመግባባት በተፈጠረ ቁጥር ውጡ እንዲባሉ፤ በአጠቃላይ ብሔር – ለብሔር የጐሪጥ እንዲተያይ እና እንዲራራቅ አይደለም፡፡ በአፍራሽ ፉክክር፣ ንትርክ እና ብጥብጥ ለመጠመድ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ነጋዴዎች እንወክለዋለን የሚሉትን ብሔር ስም እያስነሱ (እያሳመጹ) ከኪሳራ በቀር ትርፍ በሌለው የፖለቲካ ገበያ ህዝብን የሚያጋጩት ስርዓት ለመንባት አይደለም፡፡ ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ አህመድ ‹‹ኋላ ቀር›› ሲሉ የገለጹት ይህን ችግር ነው፡፡ 

 

ጉዳዩን በዚህ ደረጃ የሚመለከተው ኢህአዴግም፤ በዴሞክራሲ እና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ሊቀልድ አይገባም፡፡ የሐገራችን የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ግንባታ፤ እያደር የማሽቆልቆል አዝማሚያ መከተል ሣይሆን፤ በፍጥነት እየመጨመረ ከመጣው የህዝብ ፍላጎት ጋር አብሮ መጓዝ ይኖርበታል፡፡

 

ታዲያ እንዲህ ዓይነት ችግር የተፈጠረው፤ በየደረጃው የተቀመጡት የመንግስት እና የድርጅት የሥራ ኃላፊዎች የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ለሐገራችን ምን ያህል ወሳኝ ጉዳዮች እንደሆኑ ‹‹ባመረዳታቸው›› አይደለም፡፡ ጨርሶ አይደለም፡፡ እንዲያውም የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች የጉዳዩን አጣዳፊነት በተባ አገላለጽ በመድረክ ሲናገሩ በተደጋጋሚ መስማታችን አልቀረም፡፡ ርግጥ ነው፤ አንዳንዴ ችግሩን ‹‹በሰበብ ጋሻ›› ሊመክቱት ሲሞክሩ እናያለን፡፡ በጋሻነት ከሚነሱት ነጥቦች መካከልም አንዳንዶቹ ለችግሮቻችን ሰበብ ሆነው ሊነሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ሆኖም ሰበቦቹ ያለ ጥንቃቄ በየአጋጣሚው የሚነሱ ከመሆናቸው እና በስንፍና ለሚፈጠሩ ጉድለቶች ሁሉ ጋሻ ተደርገው የሚጠቀሱ በመሆናቸው የተነሳ፤ የህዝቡን ልብ የማሸነፍ አቅማቸው ተንጠፍጥፏል፡፡ አሁን ህዝቡ ኢህአዴግን የሚመዝነው፤ ድርጅቱ ምን ያህል ከባድ የሆኑ የትግል ምዕራፎችን አልፎ፤ ሐገሪቱን አሁን ከምትገኝበት የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረሱን ከግምት አስገብቶ አይደለም፡፡ አሁን መሪው ድርጅት እና መንግስቱ የሚመዘኑት ሊያደርጉ የሚገባቸውን ነገር በመፈጸም –አለመፈጸማቸው ብቻ ነው፡፡ 

 

ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት የተሃድሶ ንቅናቄው ሲጀመር አመራሩን ሲያስጨንቀው የነበረው እና ‹‹በጊዜ የለንም›› መንፈስ ሲያሯሩጠው የነበረው፤ በየጊዜው እንደሚወርድ ናዳ  የቆጠረው ችግር አስጊነቱ አሁንም እንዳለ ቢሆንም፤ በአመራሩ ዘንድ የነበረው ‹‹የጊዜ የለንም››  ጥድፊያ አሁን አይታይም፡፡ ሆኖም የችግሮቹ አጣዳፊነት ይበልጥ እየጨመሩ እንጂ እየቀነሱ አይደለም፡፡ በታላቅ ቁርጠኝነት የተጀመረው የዴሞክራሲ እና ልማት እንቅስቃሴ አዳዲስ ፍላጎቶችን እየፈጠረ፤ ማህበራዊ ሽግሽጉ (social mobility) እየተጠናከረ በመሄዱ፤ ዙሩ እየከረረ እንጂ እየረገበ አይደለም፡፡ ትናንት የአርሶ አደር አባቱን ህይወት ተቀብሎ ለማደር ዝግጁ የነበረው የአርሶ አደሩ ልጅ፤ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ሲወጣ ከአባቱ የተሻለ ህይወት የሚፈልግ ሰው ይሆናል፡፡ በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አዳዲስ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች እየተፈጠሩ በመሆኑ፤ ሩጫው እየከረረ እንጂ እየረገበ አይደለም፡፡ ይህ ሁኔታ ከዛሬ አስራ አምስት ዓመት በፊት ከነበረው ሁኔታ በላይ እንቅልፍ የሚነሳ ነው፡፡ የድህነቱ ናዳ እንዳለ ሆኖ፤ አሁን የልማት ናዳው ተጨምሯል፡፡ ትናንት የበጋ መንገድ ይሰራልኝ ይል የነበረው ህዝብ፤ ዛሬ የአስፋልት መንገድ አልተሰራልኝም ብሎ የሚጠይቅ ሆኗል፡፡ ሩጫው እየከረረ መጥቷል፡፡

 

በመልካም አስተዳደር ረገድ ለሚታዩት ጉድለቶች፤ የመንግስት የማስፈጸም አቅም ደካማ መሆን እንደ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችል ቢሆንም፤ ዛሬ ይህን ጉዳይ በመናገር የህዝብን ጥያቄ ማስታገስ አይቻልም፡፡ የሚቻለውን መስራት የተሳነው ሰው፤ ከአቅሙ በላይ ለሆኑ ችግሮች የሚያቀርባቸውን ምክንያቶች ተቀባይ አያገኝም፡፡ የነብር ጅራት ይዘናል፡፡ ‹‹ግዳይ እንጥላለን፤ ወይ በነብሩ እንበላለን›› የሚያሰኝ ሁኔታ ውስጥ እገኛለን፡፡ የማስፈጸም አቅማችን ደካማ ሆኖ ሳለ በቁርጠኝነት በተሰማራንበት አካባቢ ምን ዓይነት ሥራ መስራት እንደምንችል የሚያሳዩ የተግባር ተመክሮዎች አሉ፡፡ የህሊናችን ፋና ልናደርጋቸው የሚገባው እንዲህ ያሉትን ስኬቶች እንጂ፤ ሰነፎች እና ኪራይ ሰብሳቢዎች በቀላሉ አንስተው ጋሻ የሚያደርጓቸውን እጥረቶቻችን አይደለም፡፡ ከድህነት አዘቅት ወጥተው ብልጽግናን ማረጋገጥ የቻሉ ጠንካራ ህዝቦች ሁሉ እንደ ሰበብ ሊነሱ የሚችሉ ነገሮችን ተሻግረው መሄድ የቻሉ ናቸው፡፡

 

በፖለቲካው ሆነ በኢኮኖሚው እንቅስቃሴ የሚታዩ እንከኖች ሁሉ ፌዴራላዊ – ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለቀውስ የሚዳርጉ ችግሮች መሆናቸውን በመረዳት ነቅቶ መታገል ይገባል፡፡ ሃይ ባይ የሌላቸው የፓርቲ እና መንግስት ባለሥልጣናት የኢህአዴግን ፍቅር እየቸረቸሩ፤ ራሳቸው እና ከነሱ የተጠጉ ሰዎች በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚያደርጉትን ሩጫ በቆራጥ ውሳኔ መታገል ይኖርብናል፡፡

ይህ መንግስት ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› በሚል የሚጠቅሰው ችግር ተወግዶ፤  በስራ አስፈፃሚው አካል ውስጥ ያለ ባልሥልጣን የወደደውን ሐብታም የሚያደርግበት፤ የጠላውን በድህነት እንዲኖር ማድረግ የሚችልበት አሰራር እንዳይኖር በማድረግ በየደረጃው ባለው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ አድርባይነት እንዳይነግስ እና መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ በመግባቱ የተነሳ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማስወገድ የህዝብ ተሳትፎ፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ይህም ጉዳይ መልሶ ወደ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር ጉዳይ ያመጣናል፡፡ እናም በዴሞክራሲ እና በመልካም አስተዳዳር ዘርፍ ያለውን ችግር በማስወገድ የተስፋው ብርሃን እንዲደምቅ በማድረግ የተጀመረውን ፈጣን የልማት ጉዞ እናስቀጥል፡፡