የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በኢትዮጵያና ዙምባብዌ የተፈጸሙትን ጥቃቶች አወገዙ

 የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማ ፎሳ እና የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳፋቂ ማህመት በኢትዮጵያ እና በዙምባብዌ የተፈፀሙት ጥቃቶች አረመኔያዊ ሲሉ አውግዘዋል፡፡

ያለፈው ቅዳሜ ለአዳዲሶቹ ሁለት የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች አስደሳችም አሳዛኝም ሆነው ማለፋቸው ተገልጿል፡፡

መጋቢት 24፤ 2010 ዓ.ም የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን በመተካት የ42 ዓመቱ ጎልማሳ ዶክተር አብይ አህመድ መንበረ ሥልጣኑን ይዘዋል ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ በኢትዮጵያ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ስኬቶችን ለመመስከር እና ድጋፍ ለመስጠት ሰኔ 16 2010 ዓ.ም መስቀል አደባባይ በተገኙ በሚልዮን በሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መሃል እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ባደረጉበት መድረክ ቅርብ ርቀት ላይ ኢትዮጵያውያኑን ያሳዘነ ያልታሰበ የቦንብ ጥቃት ተፈፅሟል፡፡

በጥቃቱ የሁለት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ከ150 በላይ የድጋፉ ተሳታፊዎች ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

በተመሳሳይ ለረጅም ጊዜ ሥልጣን ላይ የነበሩትን የቀድሞውን የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤን ተክተው ከሰባት ወራት በፊት የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሸሙት የ75 ዓመቱ ኢመርሰን ምናንጋግዋ ሃገራቸው በቀጣይ ወር ለምታካሂደው ፕሬዝዳንታዊ እና ፓርላሜንታላዊ ምርጫ ቅዳሜ ሰኔ 16 2010 ዓ.ም ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት እሳቸው ከነበሩበት በቅርብ ርቀት ላይ የቦንብ ጥቃት ተፈፅሟል፡፡

በጥቃቱ ሁለቱም ምክትላቸው ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ሁለቱም መሪዎች ከሃገራቸውም በላይ ለአፍሪካ የፖለቲካ የምጣኔ ሃብት እና ማህበራዊ እድገት ተስፋ የተደረገባቸው መሪዎች ሆነው ሳሉ እነሱን ለማጥቃት የተደረጉት ሙከራዎች የሃገራቱን ተስፋ ለማጨለም የታቀዱ ናቸው ሲሉ የተለያዩ ሃገራት ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡

ከነዚህ ሃገራት መካከልም የደቡብ አፍሪካው  መሪ ጃኮብ ዙማን ተክተው ፕሬዝዳንት የሆኑት ሲሪል ራማ ፎሳ ናቸው፡፡

ሲሪል ራማፎሳ ጥቃቶቹ ዲሞክራሲን የሚቃወሙ የፈሪዎች እና የጨካኞች ስራ ነው ብለዋል፡፡ ከፕሬዝዳንት ኢመርሰን ምናንጋግዋ ጋር እንደተነጋገሩ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር እንደሚነጋገሩም ገልፀዋል፡፡

‹‹በዚህ በቦንብ ፍንዳታ ምክንያት ዚምባብዌን ብቻዋን አንተዋትም ከህዝቦቿ ጋር ነን፡፡ ዚምባብዌን ለማዘመን እየጣሩ ያሉት ኢመርሰን ምናጋግዋንም እንደግፋቸዋልን፡፡

 ደቡብ አፍሪካ ለኢትዮጵያ መልካሙን እንደምትመኝም ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አሳውቃቸዋለሁ፡፡ ጥቃቱ ሃገሪቱ እያደረገች ያለችውን ለውጥ የሚገታ ሳይሆን የፈሪዎቸች እና የጨካኞች ድርጊት ነው ይህ የሁለቱን ሃገራት የዲሞክራሲ ግንባታ የሚያጨናግፍ አይደለም፡፡ በአህጉራችን ላይ እየታዩ ባሉ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ እድገቶችን ለማስቀጠል በቅንጅት እንሠራለን፡፡ ››

በሁለቱም ሃገራት ላይ የተፈፀሙት ጥቃቶች ባፋጣኝ ምርመራ ተደርጎባቸው ጥቃቱ ላይ የተሳተፉትን ተጠያቂ መሆን አለባቸው ሲሉ የዘገቡት አልጀዚራ እና የደቡብ አፍሪካው ኤስ ኤ ቢ ሲ ናቸው፡