ከ163ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ አካል የሚሆኑበት 500 ትምህርት ቤቶችን ያቀፈ የትምህርት ቤት የምገባ ፕሮጀክት ይፋ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።
የትምህርት ሚኒስቴር ከህፃናት አድን ድርጅት ጋር በመሆን ሰፉ ያለ አካታች አገር በቀል የትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።
ፕሮጀክቱ በ5 ክልሎች ውስጥ ባሉ 13 ወረዳዎች ተግባራዊ እንደሚደረግም ነው የተገለፀው።
በፕሮጀክቱ ቅድመ መደበኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚካተቱ ሲሆን፣ ለአንድ አመት እንደሚቆይ ተነግሯል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ “ፕሮጀክቱ የነገ ተስፋ የሆኑ ህፃናት ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ እና በትምህርት ቤት ትምህርታቸውን በትኩረት እንዲከታተሉ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው” ብለዋል።
የህፃናት አድን ድርጅት በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ኢኪን ኦጉቶጉላሪ በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ ድርጅቱ ትኩረት አድርጎ ከሚሰራባቸው መስኮች መካከል አንዱ በመሆን በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
የምገባ ፕሮግራሙ በተፈጥሮ እና በአንዳንድ ምክንያቶች የተጎዱ እና ከዚህ በፊት ድጋፍ ያልተደረገላቸው አካባቢዎችን የሚያካትት መሆኑን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ፕሮጀክቱ ይፋ የሆነው ‘ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢዱኬሽን’ በተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት ድጋፍ አማካኝነት ነው።