93.4 ሚሊዮን መራጮች የተመዘገቡበት የናይጀሪያው ምርጫ በነገው እለት ይካሄዳል

የካቲት 17/2015 (ዋልታ) በናይጀሪያ የስልጣን ዘመናቸውን ያጠናቀቁት ሙሀመዱ ቡሃሪን ተተኪ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ በነገው እለት ምርጫ ይካሄዳል፡፡

በአፍሪካ ትልቁ ምርጫ የተባለለት የናይጀሪያ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ 93.4 ሚሊዮን ዜጎች መመዝገባቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

እ.ኤ.አ ከ1999 በኋላ ለስድስተኛ ጊዜ ለምታካሂደው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ 176 ሺሕ 846 የምርጫ ጣቢያዎች የተዘጋጁ ሲሆን ፓርቲዎቹ 360 አባላት ላሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነትም የሚወዳደሩ ይሆናል፡፡

በምርጫ 18 ፕሬዝዳንታዊ እጩዎች ለውድድር የቀረቡ ቢሆንም ሦስት እጩዎች ግን ከፍተኛ የማሸነፍ ቅድመ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡

የኮንግረስ ፓርቲ እጩ ቦላ ቲኑቡ፣ ከህዝባዊ ዴሞክራቲክ ፓርቲው አቲኩ አቡባከር እና የሰራተኞች ፓርቲው እጩ ፒተር ኦቢ በምርጫው የማሸነፍ ግምት የተሰጣቸው ናቸው፡፡