ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ ኢንዲሆን ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን – አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

ኅዳር 21/2015 (ዋልታ) ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ ይሆን ዘንድ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ታሪካዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ጥሪ አቀረቡ።

አፈ ጉባዔው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቀጣይ ዓብይ ተግባራቱን የክንውን ጊዜ ሰሌዳ ይፋ ባደረገበት ወቅት የኮሚሽኑ ቀጣይ ተግባር ስኬታማ እንዲሆን ምክር ቤቱ እያደረገ ያለውን ክትትልና ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ሪፖርቱን ያቀረቡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) እንዳሉት በቀዳሚነት ኮሚሽኑ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር መሰረት የሚሆን ምክክር ለማድረግ የሚረዱ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።

በቀጣይም እስከ ታኅሣሥ 2015 የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት፣ በጥርና የካቲት ወራት አጀንዳ ማሰባሰብ፣ ከየካቲት እስከ መጋቢት 2015 የምክክር አጀንዳዎችን ቀረፃ ማጠናቀቅ እንዲሁም በመጋቢት 2015 ዓ.ም ሀገራዊ ምክክሮች ይከናወናሉ ብለዋል።

በክልል፣ ዞን፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ፌዴራልና ዳያስፖራ በሚል በተለዩ አራት የትኩረት አቅጣጫዎች እኩል የአፈፃፀም ሥርዓት እንደሚከተልና በምክክር ሂደቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እኩል ተሳትፎና ተደማጭነት እንደሚኖራቸውም አስረድተዋል።

የቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ ከምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን እስካሁን ባለው ሂደት ኮሚሽኑ ተስፋ ሰጪ ስራዎችን ስለማከናወኑ ተጠቁሟል።

በቀጣይ የምክክሩን ተሳታፊዎች መለየት እና የአጀንዳ አሰባሰብ ሥርዓት እንዲሁም የአወያዮች መረጣን በተመለከተ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አስተያየት መስጠታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።