በተለያዩ ሀገራት የሚሠሩ ዲፕሎማቶች የሰሜን ተራራሮች ብሔራዊ ፓርክን እየጎበኙ ነዉ

ኅዳር 21/2015 (ዋልታ) በጉብኝቱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የቱሪዝም  ሚኒስትር ዴኤታ ስለሽ ግርማ እና የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ጣሂር ሙሐመድን ጨምሮ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።

አካባቢዉን አዉቆ ሀገሩን የሚያስተዋውቅ ዲፕሎማት ለመፍጠር መሰል ጉብኝቶች አስፈላጊ መሆናቸዉን የተናገሩት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሽ ግርማ፤ ጉብኝቱ በጦርነቱ እና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተቀዛቅዞ የቆየዉን የቱሪዝም መስክ ለማነቃቃት ይረዳል ብለዋል።

የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ጣሂር መሐመድ፤ ዲፕሎማቶች የሀገሪቱ የሰሜኑን ክፍል መጎብኘታቸዉ የዉጭ ሀገር ዜጎች ወደዚህ መጥተዉ እንዲጎበኙ በር ይከፍታል ማለታቸውን የዘገበው አሚኮ ነው።

ሰሞኑን በአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ስልጠና ሲወስዱ የቆዩ ዲፕሎማቶች በትላንትናዉ እለት የጎርጎራ ገበታ ለሀገርን እና የአፄ ፋሲል ቤተ – መንግሥትን ጎብኝተዋል።