ሃሰተኛ መታወቂያ ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ጥር 17/2014 (ዋልታ) በጎንደር ከተማና ዙሪያ ወረዳ 314 ሀሰተኛ የቀበሌ መታወቂያ ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት በድብቅ ሲያጓጉዙ ተገኙ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር እየሩስ አስማረ እንደገለጹት ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዱ ጥር 13 ቀን 2014 ዓም በተደረገ ክትትል በጎንደር ዙሪያ ወረዳ እንፍራዝ ከተማ 104 ሀሰተኛ መታወቂያዎችን ይዞ ተገኝቷል።

ሌላው ተጠርጣሪ ግለሰብም ጥር 14 ቀን 2014 ዓም በጎንደር ከተማ አዘዞ በሚገኘው መናኻሪያ አካባቢ 210 ሀሰተኛ መታወቂዎችን ይዞ መገኘቱን ተናግረዋል።

ከኅብረተሰቡ የደረሰ ጥቆማ መሰረት በማድረግ በፀጥታ ኃይሉ በተደረገ ጥብቅ የደኅንነት ክትትል ግለሰቦቹ ከነ ሀሰተኛ መታወቂያው እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን አስታውቀው በአጠቃላይ 314 ሀሰተኛ መታወቂያዎች በግለሰቦቹ እጅ መያዛቸውን አብራርተዋል።

ሀሰተኛ መታወቂያዎቹ በምእራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ ሽኩራ በተባለ ቀበሌ ስም የተዘጋጁና በአካባቢው ለሚንቀሳቀሱ የጠላት ኃይሎች እጅ እንዲደርሱ ለማድረግ ታስቦ የነበረ መሆኑን ዋና ኢንስፔክተሯ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ በህግ ጥላ ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመው ሀሰተኛ መታወቂያዎቹ በባሕር ዳር ከተማ በህገ-ወጥ መንገድ የታተሙ ስለመሆናቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ገልጸዋል፡፡