ግንቦት 07/2013 (ዋልታ) – በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ለሆኑ 1ሺህ 210 የአርሶ አደርና የአርሶአደር ልጆች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰጠ።
ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በመገኘት ለአርሶአደሮች እና ለአርሶአደር ልጆች የመሬት ባለቤትነት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አስረክበዋል።
በርክክብ መርሐግብር ላይ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንዳስታወቁት አርሶ አደሩን ኑሮውን ከሚመራበትና ልጆቹን ከሚያስተዳድርበት ለልማት ተብሉ መፈናቀል የለበትም ፤ለልማት እንዲውል ሲፈለግም አርሶ አደሩ ተገቢውን ካሳ አግኝቶ መሆን አለበት ብለዋል።
አርሶ አደሮች ለሃገር እድገትና ለውጥ ሲያደርጉ አቆይተዋል ፣አሁንም በማድረግ ላይ ናቸው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ አርሶ አደሩን ወደ ጎን በመተው ሳይሆን አርሶ አደሩ ከከተማው እድገት ጋር እንዲያድጉ ሲደረግነው ለውጥ የሚመጣውም ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የሚጠየቁ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መመለስና የአርሶ አሰሩን ኑሮ እንዲሻሻል ይሰራል ያሉት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የይዞታ ካርታ መሰጠቱ አርሶ አደሩ ተደራጀቶ በሚፈልገው ልማት እንዲሰማራ ያደርጋል፣ለልማት ቢፈለግ እንኳ ተገቢውን ካሳ ሳይሰጥ እንዳይነሱ ማረጋገጫ ለመስጠት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ በራሱ መሬት እና እርሻ ላይ ሰርቶ የመለወጥ መብቱ ሊረጋገጥለት እና ሊከበርለት ይገባል ያሉት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በደላሎችም ሆነ በህገወጥ መሀንዲሶች የሚደረግ ዘረፋ ሊቆም ይገባል ብለዋል ።
ዛሬ በክፍለ ከተማው የባለቤትነት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የተሰጣቸው አርሶአደሮች ተገቢውን ልማት በማካሄድ ከራሳቸው አልፈው ለከተማዋ ልማት ሊሰሩ እንደሚገባ ምክትል ከንቲባዋ አመልክተዋል።
ክፍለ ከተማው ከተመዘገቡ 7ሺህ 374 አርሶ አደሮችና የአርሶ አደር ልጆች የተመዘገቡ ሲሆን 6ሺህ 860 በትክክለኛ ማስረጃ ተረጋግጧል ፤ ከእነርሱም መካከል ለ1ሺህ 210 አርሶ አደሮች እና የአርሶ አደር ልጆች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተዘጋጅቷል።
(ምንጭ ፡-አዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪያት)