ታኅሣሥ 13/2015 (ዋልታ) በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት ምክንያት ለሁለት ዓመታት ያህል የመብራት አገልግሎት ሳታገኝ የቆየችው የሰቲት ሁመራ ከተማ ዳግም የመብራት ተጠቃሚ መሆን ቻለች፡፡
ከሁለት ዓመታት በኋላ ዳግም የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆናቸው ደስታቸውን የገለጹት የከተማዋ ነዋሪዎች በቀጣይ እንደ ንፁህ መጠጥ ውሃ ያሉ መሰረተ ልማቶች ሙሉ በሙሉ ተደራሽ እንዲሆኑም ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠይቀዋል፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው በአካባቢው በልማት ረገድ ከፍተኛ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው የመሰረተ ልማቶች ዳግም ስራ መጀመር ከተማዋን በማነቃቃት ረገድና ልማቱን በማፋጠን በኩል ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል፡፡
በዞኑ ምርት የመሰብሰብ ስራው በአብዛኛው አካባቢ የተከናወነ ሲሆን ከህብረተሰቡ የሚነሳውን የገበያ ትስስር ጥያቄ ለመቅረፍ በዋነኝነት በአኩሪ አተርና በማሾ ምርት ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ከአካባቢው አልሚዎች ጋር በጋራ ቢሰሩ አትራፊ እንደሚሆኑ ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡
ሳሙኤል ሓጎስ (ከሰቲት ሁመራ)