መጋቢት 30/2014 (ዋልታ) የንባብ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሦስት ወራት የሆነው አብሮኆት ቤተ መፅሐፍ ከግለሰቦችና ከተለያዩ ተቋማት 7 ሺሕ 3 88 መፅሐፍት ተበርከቶለታል፡፡
በለንደን የ ፒ ኤች ዲ ተማሪ የሆኑት ቤተልሄም ሠለሞን 5 ሺሕ 200 መፅሐፍት ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን በገንዘብ ሲተመን 5.5 ሚሊዮን ብር ያወጣል ተብሏል፡፡
በተመሳሳይም የአድዋ መድኃኒት ቤት ባለቤት አምባሳደር ማርቆስ ኢንሳይክሎፒዲያን ጨምሮ 904፣ የአዲስ አበባ መምህር የነበሩና ህይወታቸው ያለፈ ግለሰብ ከቤተሰቦቻቸው 997 እንዲሁም ማይክሮሊንክ የተባለ ተቋም 287 መፅሐፍት አበርክተዋል።
ቤተ መፅሐፍቱ ዛሬ የተደረገለት የመፅሐፍ ድጋፍን ጨምሮ እስካሁን 12 ሺሕ መፅሐፍት ድጋፍ ተደርጎለታል።
ለቤተመፅሐፍቱ በተደረገው ድጋፍ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ተገኝተዋል።
መፅሐፍት በመስጠትና በማካፈል ትውልድን ማነፅ የሚቻል መሆኑ የዛሬው የመፅሐፍ ድጋፍ ማሳያ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽሕፈት ቤታቸው አማካኝነት ለአንድ ወር የሚቆይ በመላው ዓለም የመፅሐፍት ማሰባሰብ ተግባር ይከናወናል ሲሉ ገልፀዋል።
በምንይሉ ደስይበለው