መጋቢት 04/2013 (ዋልታ) – 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ወጣቶች ህይወታቸውን ሳይሆን ድምፃቸውን የሚሰጡበት ሊሆን እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
ለዚህም ደግሞ ወጣቶች በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና በሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ ያላቸውን አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ተጠይቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ለቂርቆስና ልደታ ክፍለ ከተማ ወጣቶች የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጡ የሚያስችል የ’ማይንድ ሴት’ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከጭፍን ጥላቻ ውጪ በመሆን ነገሮችን መመዘን የሚችል ወጣት ማፍራት ያስፈልጋል ተብሏል።
ባለፉት ጊዜያት ኢትዮጵያ የህዝብ ለህዝብ ግጭት ውስጥ እንድትገባ ሲሰራ ቆይቷል፤ ወጣቱ ግን በማያግባቡ ትርክቶች ላይ በግልፅ በመነገጋገር የመፍትሄ አካል ሊሆን ይገባል ተብሏል።
የኢትዮጵያችን ከፍታ በእኛ ወጣቶች ሁለንተናዊ የነቃ ተሳትፎ ይረጋገጣል በሚል መሪ ሀሳብ የስልጠና መርሀግብሩ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
(በትዕግስት ዘላለም)