ግንቦት 26/2013 (ዋልታ) – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ለሚገኙ የተለያዩ ዲፕሎማቶች በትግራይ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ እና እየተሰራ ስላለው የመልሶ ግንባታ ስራ ገለጻ አድርጓል፡፡
በአሸባሪው የህወሓት ቡድን የወደመውን መሰረተ ልማት መንግስት ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ እየሰራ መሆኑን እና ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ተቋማት ጋር በመሆን የሰብዓዊ እርዳታ ስራዎች መከናወናቸው ተጠቁሟል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአሁኑ ሰዓት ትግራይ ክልልን በተመለከተ የሀሰተኛ መረጃ እየተሰራጨ በመሆኑ ዲፕሎማቶች ምንም አይነት ጥያቄ ቢኖራቸው መንግስት ትክክለኛውን መረጃ ይሰጣል ብለዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው፣ በትግራይ ክልል እየተደረገ ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍ እና የመልሶ ግንባታ ስራ ለዲፕሎማቶቹ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል መንግስት እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እየተንቀሳቀሱ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን እና ከግብርና ስራ ጋር ተያይዞ ምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት በተለያዩ የክልሉ ከተሞች እየተሰራጩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ ትምህርት ሚኒስቴርም በክልሉ ከፍተኛ ገንዘብ በመበጀት የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ በክልሉ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ መከናወኑን እና እየተደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ እና ሌሎች ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በህግ ማስከበር ሂደቱ ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የጾታ ጥቃት የፈጸሙ ወታደሮች በህግ አግባብ ተጠያቂ መደረጋቸውም ነው የተገለጸው፡፡
(በሜሮን መስፍን)