ሚኒስቴሩ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ የክረምት በጎ አድራጎት መርኃግብር በይፋ ተጀመረ

ሰኔ 29/2013 (ዋልታ) – የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የአቅመ ደካሞችን ቤቶች በማደስ በትምህርት ዘርፉ የሚካሄደውን የክረምት የበጎ አድራጎት መርኃግብርን በይፋ አስጀምረዋል።

በበጎ አድራጎት መርሀ ግብሩም በትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ በክፍለ ከተማው 15 የአቅመ ደካሞች ቤት እንደሚታደስም ተገልጿል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆነው የመተጋገዝ እና የመደጋገፍ ባህልን መሰረት በማድረግ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ በመቻላችን ደስታ ይሰማናል ብለዋል።

በሁለት ሳምንት ውስጥ ቤቶቹን በማደስ ለነዋሪዎቹ እንደሚያስረክቡም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ለአቅመ ደካሞቹም ቤቱን ከማደስ ባሻገር አስፈላጊ የቤት እቃዎችም እንደሚሟሉ ተገልጿል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ ተማሪዎች በክረምቱ መርኃግብር በየአካባቢያቸው በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች በመሳተፍ ከወገን አልፈው ሀገርን የማገዝ ሀላፊነታቸውን በንቃት እንዲወጡ ሚኒስትሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።