ግንቦት 13/2013 (ዋልታ) – ለ2013/14 ዓ.ም የምርት ዘመን የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚውሉ የምርጥ ዘር፣ ኬሚካልና የአፈር ማዳበሪያ ግብዓቶችን በወቅቱ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለክልሎች ማሰራጨት መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የግብርና ግብዓትና ግብይት ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ተስፋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ ለ2013/14 ዓ.ም የእርሻ ዘመን የተሻለ ምርት ለማምረት የሚረዱ የአፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና የኬሚካል አቅርቦትን ማቅረብ ችሏል፡፡
የቅድመ መኸር ዝግጅት ላይ 18 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ ሀገር መገዛቱን ጠቁመው፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የተፈጠረውን ቅንጅታዊ አሠራር በመጠቀም 11 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል ጅቡቲ ወደብ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ጅቡቲ ወደብ ከደረሰው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ፤ አስር ነጥብ አምስት ሚሊየን ኩንታል ተጓጉዞ ወደ ሀገር ውስጥ ገቢ ተደርጓል፡፡
ለአማራ፣ ለኦሮሚያ፣ ለደቡብ ህዝቦች፣ ለሲዳማ፣ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝና ለትግራይ ክልሎች የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮዎች በጥያቄያቸው መሰረት ተሰራጭቷል ብለዋል፡፡
የአፋር፣ ሶማሌ፣ ሐረር፣ ጋምቤላ ክልሎች ማዳበሪያውን የማሰራጨት ሂደቱ በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ የምርጥ ዘር አቅርቦት በሀገር ውስጥ የሚመረት እንደሆነና እስከአሁን ድረስ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን ኩንታል የተበጠረና ጥራቱን የጠበቀ ምርጥ ዘር መቅረቡን አመልክተዋል፡፡
ኬሚካል አቅርቦትን አስመልክተውም፤ የዘንድሮ ፍላጎት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ሊትር መሆኑን የገለጹት አቶ መንግሥቱ፣ ግዢው እንደተጠናቀቀ ለአርሶ አደሩ የማቅረብ ሥራ የሚሠራ ይሆናል ብለዋል፡፡