የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሊት በተያዘለት ጊዜ እንደሚካሄድ አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ

ግንቦት 13/2013 (ዋልታ) – የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሊት በሶስቱ ሀገራት የሳይንቲስቶች ብሄራዊ ቡድን ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በተያዘለት ጊዜ እንደሚካሄድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ሚኒስትሩ በጎረቤት አገራትና ታላላቅ ሃይቆች ክልል የሚገኙ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሚሲዮኖች ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር “የናይል ፍትሃዊ አጠቃቀም፣ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ለክልላዊ ትብብር ያለው ሚና” በሚል ርእስ በተዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት ላይ ተሳትፈዋል።
ግብፅና ሱዳን ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
የሶስትዮሽ ድርድሩ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ መርህ መሰረት ውጤታማ እንዲሆን የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን እምነት አረጋግጠዋል።
የደቡብ ሱዳን ምክትል የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ጉዳዮች ሚኒስትር ደንግ ዳው ደንግ በበኩላቸው፣ ታላቂ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የሰላም ፕሮጀክት መሆኑን ገልፀዋል። አያይዘውም የደቡብ ሱዳን ፓርላማ በቅርቡ የናይል ስምምነት ማዕቀፍን (CFA) በቅርቡ እንደሚያፀድቅ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሶሰትዮሽ ድርድር ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ በመድረስ እልባት እንደሚያገኝ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
በወቅቱም የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋውና ሌሌች የዘርፉ ባለሙያዎች የውይይቱን መነሻ ፅሑፍ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።