ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለ300 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገለጸ

ነሐሴ 7/2015 (አዲስ ዋልታ) ቱሪዝም ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ በመሳተፍ ድጋፍ ለሚሹ 300 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገለጸ።

የሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች የትምህርት ቁሳቁሱን ካበረከቱ በኋላ በአብራሞ ወረዳ ለሚያስገነቡት ቤተ-መጻህፍት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እንደገለጹት በሀገሪቱ እየተካሄደ ባለው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት መጠነ ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡

በተለይም በክረምት በጎ ፈቃድ የሚካሄደው የ”ትምህርት ለትውልድ” መርሃ-ግብር በትምህርት ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላት የመማር ማስተማሩን ሂደት ለመደገፍ አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን በመሙላት ሃገር ተረካቢ ለሆኑ ህጻናት የተሻለ የትምህርት አካባቢ መፍጠር የቁሳቁስና ሌሎች ግብዓቶችን በማሟላት የትምህርት መርሃ-ግብር እንዲጠናከር አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር ትምህርት ቤቶች ቁልፍ መሆናቸውን ጠቅሰው በክልሉ በክረምት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የትምህርት ተቋማትና የተማሪዎችን አቅም ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው በዚህ በኩል ክልሉ ተጨማሪ ስራዎች እንደሚጠብቁት አክለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ተጠሪ ተቋማት ለክልሉ ያሳዩት አለኝታነት የክልሉ መንግስትና ህዝብን ያኮራ መሆኑን ርእሰ መስተዳደሩ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡