ታኅሣሥ 17/2015 (ዋልታ) በዲፕሎማሲው ዘርፍ የኢትዮጵያ ህዝብን የሚመጥንና ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቁ ተግባራት ተከናውነዋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በዓመታዊ የሚሲየን መሪዎች ስብሰባና ስልጠና መክፈቻ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ጉዞ ኢትዮጵያ የላቀ ስኬትና ድል እንድታስመዘግብ በውጭ ግንኙነት ጥሩ እምርታዎች ማስመዝገብ እንደተቻለ የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የውጭ ግንኙነቱ በፈተናዎች የታጀበ መሆኑንም አመላክተዋል።
በሀገር ውስጥ የነበሩ ፈተናዎች የማለዘብና የማስገንዘብ ስራዎችን በመስራት በውጭ ግንኙነት የገጠሙ ፈተናዎችን ለመቀነስ መቻሉንም አንስተዋል።
ወዳጅን በማብዛትና አጋር በማስፋት የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ በተሰሩ ስራዎች ውጤት አግኝተናል ያሉት ሚኒስትሩ በዚህ በኩል በተለየዩ አገራት የተወከሉ ሚሲዮኖች የነበራቸው ሚና የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሁን ደግሞ ሀገራችንን በሚመጥን ተግባር ላይ መሰማራት የሚገባ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎችና የሚሲዮን መሪዎች ዓመታዊ ስብሰባና ስልጠና መካሄድ ጀምሯል።
በሰለሞን በየነ