ምርጫ ቦርድ ብልፅግና ፓርቲ ተጨማሪ መረጃዎችን እንዲያቀርብ ጠየቀ

ሚያዝያ 19/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብልፅግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን በተመለከተ ተጨማሪ ሰነዶች እና መረጃዎችን እንዲያቀርብ ጠየቀ፡፡

ቦርዱ የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤውን ሂደት፣ በጉባኤው የተወሰኑ ውሳኔዎችና የተደረጉ ምርጫዎችን በተመለከተ ከህጉ አንፃር ለመወሰን ተጨማሪ ሰነዶችና መረጃዎች ማየት በማስፈለጉ እስከ ሚያዝያ 25/2014 ዓ.ም ድረስ እንዲያቀርብ ነው የጠየቀው፡፡

ቦርዱ ሚያዝያ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ፓርቲው ያቀረባቸውን የጠቅላላ ጉባኤ ሰነዶች እና ጠቅላላ ጉባኤውን በታዘቡት የቦርዱ ተወካዮች የቀረበውን ሪፖርት መመርመሩን አስታውቋል።

ይሁንና የጠቅላላ ጉባኤውን ሂደት፣ በጉባኤው የተላለፉ ውሳኔዎች እና የተደረጉ ምርጫዎችን በተመለከተ ከሕጉ አንጻር ለወሰን ተጨማሪ ሰነዶች እና መረጃዎችን ማየት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሟል።

በመሆኑም ፓርቲው ምርጫ ቦርድ በዝርዝር ያስቀመጣቸውን ጉዳዮች ከሚያያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም በፊት ለቦርዱ እንዲያቀርብ አሳውቋል።

ቃለ ጉባኤን በተመለከተ፣ በጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤው ላይ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባው ምልአተ ጉባኤ ተሟልቷል ቢባልም በግልፅ የጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊ አባላት ብዛት ስላልተቀመጠ ተገልፆ እንዲቀርብ፤ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የተጠቆሙበት ሂደት፣ እነማን እንደተጠቆሙ፣ ከተጠቆሙት ውስጥ የተመረጡት አባላት እያንዳንዳቸው በስንት ድምፅ እንደተመረጡ በጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ ውስጥ ያልተገለፀ በመሆኑ ይሄው ተካትቶ እና ተረጋግጦ እንዲቀርብ፤ በፓርቲው የቀረበው ጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ በፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተፈርሞ እንዲቀርብ፤ የማዕከላዊ ኮሚቴው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን የመረጠበትን ሂደት የሚያሳይ የማዕከላዊ ኮሚቴ ቃለ ጉባኤ ስላልቀረበ እንዲቀርብ ጠይቋል።

የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብን በተመለከተ ደግሞ በመተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 18/3 መሠረት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ብዛት እና ስብጥርን በተለከተ የወጣ የአፈፃፀም መመሪያ ካለ የመመሪያውን ኮፒ ማዕከላዊ ኮሚቴው መመሪያውን ካፀደቀበት ቃለ ጉባኤ ጭምር እንዲቀርብ ምርጫ ቦርድ ለፓርቲው በጻፈው ደብዳቤ መጠየቁን ከቦርዱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።