ሰኔ 07/2013 (ዋልታ) – የፊታችን ሰኞ የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፌዴራል እና የክልል የደህንነትና የፀጥታ መዋቅር በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን የብሔራዊ ደህንነትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የፌዴራል እና የክልል የደህንነት እና የፀጥታ አካላት ግብርሃይል በወቅታዊ የሀገሪቷን ደህንነት የሚገመግም እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ ውይይት እያደረጉ ነው።
በውይይቱ ወቅት የብሔራዊ ደህንነት እና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ቀጣዩ የምርጫ እና ድህረ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
ምርጫውን እና የግድቡን ሙሌት ለማስተጓጎል የሚሰሩ የውጭ እና የውስጥ ጠላቶች መኖራቸውን የተናገሩት አቶ ተመስገን ከደህንነት መስሪያ ቤቱ ክትትል አያመልጡም ብለዋል።
እንደ ኢብኮ ዘገባ የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ እና ደህንነት አካላት የጋራ ግብረ ሀይልም የሀገሪቷን ወቅታዊ የደህንነት ሁኔታ በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣሉ ተብሏል።