ምክር ቤቱ የሕዝቦችን ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ በኩል ክፍተት ነበረበት ተባለ

ሚያዝያ 15 /2013 (ዋልታ) – የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝቦችን ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ በኩል ክፍተት ነበረበት ተባለ፡፡

ምክር ቤቱ ዜጎች እኩል መልማት እና በተናጠል ኢኮኖሚያዊ መሻሻሎች እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያስችሉ 5 ጥናቶች ማድረጉ ተገልጿል፡፡

ጥናቱም በነገው የተሻለ ተስፋ ላይ ተመርኩዞ ጉድለቶችን ለመሙላት ያለመ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ፍትሃዊ ውክልና የሚረጋገጥበት ተቋም በመሆኑ የተሰጠው ተግባር እና ኃላፊነት ፍትሃዊነትን ከማረጋገጥ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተያያዙ ናቸውም ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ የፌዴራሊዝምን የመንግሥት አስተዳደር መከተል ከጀመረች አመታትን ብታስቆጥርም የህዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሊያስከብር የሚገባው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይህን ኃላፊነቱን ሳይወጣ መቆየቱ ይገለፃል፡፡

ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም ቅሉ አሁን ይህን ማስተካከል በማስፈለጉ ምክር ቤቱ በአምስት ዋና ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ጥናት አካሂዷል፡፡ በጥናቱ ላይ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና የምክር ቤቱ አባላት በተገኙበት ምክክር ተደርጓል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የራሱን አደረጀጃት የሚፈትሽበት፣ ማህበረሰቡ በልዩነት ውስጥ አንድ ሆኖ የሚኖርበትን፣ የህግ መንግስት የበላይነት፤ የዜጎችን ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነት የሚመለከቱት ጉዳዮች በጥናቱ ተካተዋል፡፡

የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የምክር ቤቱ ሃላፊነት መሆኑን ተከትሎ በተለያዩ አከባቢዎች ላይ የሚስተዋሉ ጉድለቶች ለመሙሏት ነገን ማሳብ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

የዜጎች ፍትሓዊ የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት እና በተናጠል ደግሞ የምጣኔ ሃብትና ማኅበራዊ መሻሻሎች እንዲኖራቸው ተከታትሎ የሚያስፈፅም ገለልተኛ አካል ያስፈልጋልም ተብሏል፡፡

ይህን የማስፈፀም ስልጣኑ ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የተደረጉ ጥናቶች ለዚህ መደላድል የሚፈጥሩ እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡
(በሚኪያስ አዱኛ)