ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ከ15 ሺሕ በላይ መጻሕፍትን ለአብርሆት አበረከተ

ሰኔ 13/2014 (ዋልታ) ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ከ15 ሺሕ በላይ መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት አበርክቷል።
“ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በሚከናወነው የመጻሕፍት ማሰባሰብ ንቅናቄ የተለያዩ ተቋማትና ዜጎች ሚናቸውን እየተወጡ ነው።
የሰላሌ ዩኒቨርሲቲም 15 ሺሕ መጻሕፍትን በዛሬው ዕለት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት አበርክቷል።
መጻሕፍቱን የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት እሸቱ ወንድሙ (ዶ/ር) ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ተወካይ ታምራት ሃይሌ (ዶ/ር) አስረክበዋል፡፡
መጻሕፍቱ በጤና፣ በህዋ ሳይንስ፣ በምህንድስና እንዲሁም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
መጻሕፍቱን የተረከቡት የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ተወካይ ታምራት ሃይሌ ለአብርሆት ቤተመጻሕፍት እየተደረገ ያለው የመጻሕፍት ማሰባሰብ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ዩኒቨሲቲው ላበረከታቸው መጻሕፍትም ምስጋና አቅርበው በቀጣይም ሌሎች ዜጎችና ተቋማት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ ዜና የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ በግላቸው በኦሮምኛ ቋንቋ የደረሷቸውን የሰዋሰውና የተረት ይዘት ያላቸው 50 መጻሕፍትን ለአብርሆት አበርክተዋል፡፡
መጻሕፍቱ ሀገር በቀል እውቀትን ለማስፋፋትና በኦሮምኛ ቋንቋ ተረቶችና ሰዋሰው ላይ ለሚመራመሩና ለሚማሩ አጋዥ ሆነው እንደሚያገለግሉ ጠቅሰዋል።