ሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ የቴሌኮም ሥራውን በተያዘለት ጊዜ ለመጀመር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

ነሐሴ 26/2013 (ዋልታ) – ሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በገባው ውል መሠረት የቴሌኮም ሥራውን በፈረንጆቹ 2022 ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ  መሆኑን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አስታወቁ።

ይህንን ግብ ለማሳካትም እየተደረጉ ስላሉ ዝግጅቶችን በተመለከተም  ለኢፌዲሪ ገንዘብ ሚኒስቴር አመራሮች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ እና ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር ፒተር ንዴግዋ በተመራው የሳፋሪኮም እና የሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ልዑካን ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ ሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ በሀገሪቱ ውስጥ ስለሚያከናውነው ኢንቨስትመንት ሂደቶች እስካሁን የተከናወኑ ተግባራት እና በቀጣይነት ስለሚከናወኑ ሥራዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ኩባንያቸው አገልግሎቱን በአፋጣኝ ለመጀመር ኢትዮ-ቴሌኮምን ጨምሮ ከሌሎች የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን የሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር ፒተር ንዴግዋ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ጥራት፣ ተደራሽነት እና ፈጠራ ላይ የተሻሻሉ ውጤቶችን ለማምጣት ለሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ገልጸዋል።

መንግሥት በሀገሪቱ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ለሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች የተጠናከረ ድጋፍ ለማድረግ የገባውን ቃል እንደሚቀጥልም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ በሚያደርገው ኢንቨስትመንት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሚቆጠሩ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።