ግንቦት 23/2013 (ዋልታ) – የአሜሪካው ሴናተር ጂም ኢንሆፌን ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፌስቡክ ገፃቸው “የኢትዮጵያውያን ወዳጅ የሆኑት የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተር፣ ጂም ኢንሆፌን ወደ ሁለተኛው ቤትዎ ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጡ እላለሁ” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሴናተሩ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ እያሳደረ ያለውን ጫናና እና የጉዞ ማዕቀብ በመቃወም በዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ሴናተሩ በንግግራቸው አሸባሪውን ሕወሃትና የኢትዮጵያ መንግሥት በእኩል ዓይን ለማየት መሞከር ተገቢ አይደለም ሲሉም ተደምጠው ነበር፡፡
የአሜሪካው ሪፐብሊካን ፓርቲሴናተር ጂም ኢንሆፍ በአሜሪካ ለምክር ቤቱ የኢትዮጵያ መንግስትን ከሽብርተኛው ድርጅት ሕወሓት ጋር በተመሳሳይ ረድፍ ለማስቀመጥ መሞከር ተቀባይነት የለውም ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ሴናተሩ በጽሑፋቸው “የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉንም ሰላማዊ መፍትሔዎችን ለማምጣት እየሰራ ይገኛል፤ ሰላምንና አንድነትን ከማምጣት ውጪ ሌላ አካሄድ አልሄደም” ብለዋል።
ኢትዮጵያን ለ19 ጊዜያት ያህል ጎብኝቻለሁ ያሉት ሴናተሩ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በነበራቸው ቆይታ መንግስት በአገሪቱ አንድነትንና ሰላምን ለማምጣት እየሰራ መሆኑን መነጋገራቸውን ለምክር ቤቱ ማስረዳታቸው ይታወሳል፡፡