ስራ አጥነትን ለመቅረፍ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን ማጠናከር ያስፈልጋል ተባለ

ግንቦት 18/2014 (ዋልታ) የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን ማጠናከር ያስፈልጋል ሲሉ የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን ተናገሩ።

የክልል እና ከተማ አስተዳደሮች የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ አስተባባሪዎች አገር አቀፍ የውይይት መድረክ በባህር ዳር  ከተማ እየተካሄደ ነው።

የውይይት መድረኩ በስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የተዘጋጀ ሲሆን የአንድ ማዕከል ብቃት ለስራ እድል ፈጠራ  ውጤታማነት በሚል ነዉ እየተካሄደ  የሚገኘው።

በመድረኩ የታደሙት የስራ እና ክህሎት  ሚኒስቴር የስራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ  ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሡ ጥላሁን፤ እንደ ሀገር ያለውን የስራ አጥነት  ችግር ለመቅረፍ የአንድ ማዕከል አገልግሎት  መስጫ ጣቢያዎችን ማጠናከር አስፈላጊ ነው ብለዋል።

መድረኩም የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ አስተባባሪዎችን እና የዘርፉ ልማት አመራሮችን አቅም በመገንባት ስራ አጥነትን መቅረፍ አላማ ያደረገ ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።

ከወረዳ እስከ  ፌዴራል  ያሉ የአንድ ማዕከል አገልግሎት  መስጫ ጣቢያዎች ያሉባቸውን ችግሮች ለመለየት እና መፍትሄ ለመስጠት የሚያግዝ ነውም  ተብሏል።

በውይይት መድረኩ ከአማራ፣ ከሲዳማ፣ ከአፋር፣ ከሶማሌ እና ከቤንሻንጉል ጉሙዝ  ክልሎች  እንዲሁም ከአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር የመጡ የአንድ ማዕከል  አገልግሎት  መስጫ ጣቢያ አስተባባሪዎች እና ሌሎች  ባለድርሻ አካላት  እየተሳተፉ ነው።

አገር አቀፉ የውይይት መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ነው ተብሏል።

የሻምበል ባምላኩ (ከባህር ዳር)