ቀሪና ድጋሚ ጠቅላላ ምርጫ በሚካሄድባቸው ክልሎች የድምጽ መስጫ ወረቀት እየተጓጓዘ ነው – ምርጫ ቦርድ


ሰኔ 4/2016 (አዲስ ዋልታ) የስድስተኛው ዙር ቀሪና ድጋሚ ጠቅላላ ምርጫ በሚካሄድባቸው ክልሎች የድምፅ መስጫ ወረቀት ሚስጥራዊነቱ ተጠብቆ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች መጓጓዝ መጀመሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሰኔ 2013 ዓ.ም እና መስከረም 2014 ዓ.ም 6ኛ ዙር ጠቅላላ ምርጫ መካሄዱን አስታውሰው በጸጥታ ምክንያት ምርጫ ያልተካሄደባቸው እንዲሁም ድጋሚ ምርጫ የሚደረግባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

በዚህም በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያና ሶማሌ ክልሎች በ29 የምርጫ ክልሎች የቀሪና ድጋሚ ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና አፋር ቀሪ ምርጫ ሶማሌ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ድጋሚ ምርጫ የሚደረግባቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ቦርዱ ተወዳዳሪ እጩዎችን አጣርቶ በመለየት የጊዜ ሰሌዳ በማውጣት በክልሎች ከሚወዳደሩ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ማድረጉንም ተናግረዋል።

የመራጮችና እጩዎች ምዝገባን እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መስቃን እና ማረቆ እንዲሁም በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ የመራጮች ምዝገባ በድምፅ መስጫው ቀን ይከናወናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የራሱን ቡድን በማዋቀርና ከተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመመካከር በአራቱም ክልሎች ምርጫ ማከናወን የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን አረጋግጠናል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከዚህም ባሻገር የምርጫ ወረቀቶች ሚስጥራዊነታቸው ተጠብቆ ከውጭ ታትመው በከፍተኛ ጥንቃቄ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እንዲጓጓዙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ 7 ድርጅቶች ታዛቢዎችን ለማሰማራት ጥያቄ አቅርበዋልም ብለዋል፡፡

ምርጫውን ለማካሄድ 1 ሺሕ 285 ምርጫ ጣቢያዎችና 6 ሺሕ 380 ምርጫ አስፈፃሚዎች መዘጋጀታቸውንና በአራቱ ክልሎች ለሚወዳደሩ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች በድምሩ 21 ሚሊየን ብር ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።