በ19ኛዉ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፈዉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ሽልማት ተበረከተለት


ነሐሴ 25/2015 (አዲስ ዋልታ) በሀንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደዉ በ19ኛዉ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ ቡድን የገንዘብና የእውቅና ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡

ፌዴሬሽኑ በዛሬዉ ዕለት የሽልማት እና የእዉቅና መርሀ ግብር አካሂዷል።

በዚህም የወርቅ ሜዳሊያ ላመጡ አትሌቶች 60ሺህ ብር፣ የብር ሜዳሊያ ላስገኙ 40 ሺህ ብር፣ የነሀስ ሜዳሊያ ላመጡ አትሌቶች ደግሞ የ20ሺህ ብር ሽልማት በፌዴሬሽኑ ተበርክቷል።

በተጨማሪም በልዩ ተሸላሚ ዘርፍ የማራቶን አትሌቶቹ የአለምዘርፍ የኋላዉ እና አትሌት ፀሀይ ገመቹ 50 ሺህ ብር ተሸልመዋል፡፡

በአጠቃላይ 1.8 ሚሊየን ብር ሽልማት ለአትሌቲክስ ልዑክ ቡድኑ መበርከቱም ተመላክቷል፡፡

በመርሀ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ባህልና ስፓርት ሚኒስትር ሚኒስቴር ቀጀላ መርዳሳን ጨምሮ የፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

ኢትዮጵያ በ19ኛዉ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳትፎ 2 የወርቅ፣ 4 የብር እና 3 የነሀስ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከአፍሪካ 2ተኛ ከአለም ደግሞ 6ተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡

በመሰረት ተስፋዬ