በውሃ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉትን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በአግባቡ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል – አምባሳደር ስለሺ በቀለ

አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)

ነሐሴ 25/2015(አዲስ ዋልታ) በውሃ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉትን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለማስተዋወቅ አመታዊ ኤግዚቢሽኖችን ከሌሎች ፕሮግራሞች ጋር እያስተሳሰሩ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ገለጹ።

አምባሳደሩ በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ያለውን የውሃና ኢነርጂ አውደ ርዕይ ዛሬ ጎብኝተዋል።

ደመናን በማበልጸግ እንዴት ዝናብ ማግኘት እንደሚቻልና ለተለያዩ ጠቀሜታዎች እንደሚውል፤ በተቃራኒው መሬት በአግባቡ ካልተጠበቀ በዝናቡ ምክንያት የሚደርሰውን የመሬት መሸርሸርና ተያያዥ ችግሮች የሚገልጹ ሁኔታዎች በአውደ ርዕዩ እየታዩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ያለውሃ መኖር አይቻልም ሁለት ሶስተኛው አካላችን ውሃ ነው ያሉት አምባሳደሩ አውደ ርዕዩ የውሃ ሀብት አጠቀቃምና ቴክኖሎጂዎችን እንደሚያስተዋውቅ አመልክተዋል።

አክለውም አውደ ርዕዩ የውሃ ሀብት ለመጠጥ ብቻ ሳይሆን ለምግብ ማምረት ያለውን ጠቀሜታ፣ ለሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል እንዴት እንደሚውል፣ እንዲሁም የተለያዩ ግድቦችን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በግሉ ዘርፍም በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች እያመረቱ መሆኑን ለማየት መቻላቸውን ገልጸዋል።

የዚህ አይነቱ አውደ ርዕይ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ ተግባራትን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ሁሉም የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት መነቃቃትን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

በአውደ ርዕዩ የቀረቡት ስራዎች ከአሁን በፊት በዚህ ልክ ተሰርተው አያውቁም ያሉት አምባሳደሩ አዳዲስ ስራዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ ዓመታዊ ኤግዚቢሽን ከሌሎች ፕሮግራሞች ጋር እያስተሳሰሩ ማቅረብ ቢቻል መልካም ነው ሲሉም ምክረ ሀሳብ ማቅረባቸውን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።