ሰኔ 18/2013 (ዋልታ) – በትግራይ ወጣቶች ላይ የተቃጣ እና ወጣቶች በክልላቸውና በአገራቸው ጉዳይ ላይ በአዎንታዊ አግባብ የሚያደርጉትን የነቃ ተሳትፎና አበረታች ጅማሬ ለማሸማቀቅ የተዘረጉ የጥፋት በትሮችን ከፀጥታና የደህንነት አካላት ጋር በተቀናጀ እርምጃ ለማክሸፍ እንደሚሰራ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በእንጅነር እምብዛ ታደሰ እና ባለፋት ተከታታይ ወራት በክልሉ በንፁሐን አገልግሎት ሰጪ ሰራተኞች ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ጥቃቶችን በጥብቅ በማውገዝ በእንጅነር እምብዛ ታደሰ አሰቃቂ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ከሁለት ቀናት በፊት በመቐለ ከተማ በግምት ከቀኑ ሰባት ሰዓት በኃላ ወጣት እንጅነር እምብዛ ታደሰ ከቢሮ ወደ መቀሌ አሉላ አባ ነጋ የአየር ማረፊያ ለመጓዝ በተዘጋጀበት፣ ለግዜው ማንነታቸው ባልታወቁ አፋኞች በሐይል ተወስዶ ደብዛው ጠፍቶ ነበር።
በፌደራል ፖሊስ የፀጥታ ሐይሎች በተከናወነ አሰሳ እንጅነር እምብዛ በጨካኝ የከተማ ሽብር ተልእኮ አስፈፃሚ ወንጀለኞች በዓይደር ልዩ ስሙ ማረምያ ቤት በተባለ ስፍራ ተገድሎ ለጅቦች ከተጣለበት ስፍራ ትላንት ከረፋዱ አምስት ሰዓት ቁርጥራጭ የሰውነት አካላቱን በመለየት በተጨማሪ ምርመራም፤ በጭካኔ መገደሉን ማረጋገጥ መቻሉን መግለጫው አትቷል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሰጠው ሙሉ መግለጫ
————————————–
“ትግራይ! የቁርጥ ቀን የነፍስ አድን ልጆችዋን ለመከራ ነጋዴዎች አትገብርም”!
በትግራይ የንፁሐን ዜጎችን ሰቆቃን የማስቆም፤ ተጨማሪ የህይወት መጥፋት እንዳይከሰት አጥብቆ የመስራት ጉዳይ፣ አሁንም በርካታ ፈተናዎች ያሉበትንና የልዩ ልዮ ተዋናዮች ተግባራትም ቢያንስ፣ በሰብአዊነትና ነፍስን በማዳን ጉዳይ ላይ አግባቢ ሊሆን ይገባ ነበር። ሆኖም በተጨባጭ ከእለት ወደ እለት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ስንመለከት ከሰብአዊነትና ከተለመደ የማህበራዊ ሁኔታ ልምምዶች ያፈነገጡ መሆናቸውን ስንታዘብ ግን በእጅጉ የተለየና አሳዛኝ መሆኑን እንረዳለን።
በትግራይ በሚካሔዱ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በተመለከተ፣ በማህበራዊ ሚዲያና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች በአንዳንድ የታጣቂ ቡድኑ የጦር አመራሮች ከሰሞኑ ታቅደው በተከታታይ የተላለፋ የዘመቻ ውጤቶች ቃለ ምልልሶች፤ የራሳቸው የተለየ አላማን ለማስፈፀም የተዘረጉ ንፁሃንን ሰለባ የሚያደርግ አደገኛ የሰለባነት ትርክቶች ናቸው።
እነዚህ የበቀልና ዛቻ ጥሪዎች ፣ የትግራይን የቁርጥ ቀን ወጣት የነፍስ አድን ሙያተኞች ህይወት ጭካኔ በተሞላበት መንገድ መንጠቅ መጀመራቸውን ተከታታይ መርዶዎች በቁጭት ፣ በእልህና በጥልቅ ሀዘን ስናረዳ ፣ የምላሹ መቋጫና መላም እጅግ የፈጠነ ፣ የተሰላና አስተማሪ የሚሆን መሆኑን ለአጥፊዎች ከወዲሁ በጥብቅ በማስገንዘብም ጭምር ነው።
ከሁለት ቀናት በፊት በመቐለ ከተማ በግምት ከቀኑ ሰባት ሰዓት በኃላ ባለው ግዜ ፣ ከቢሮ ወደ መቀሌ አሉላ አባ ነጋ የአየር ማረፊያ ለመጓዝ በተዘጋጀበት፣ ለግዜው ማንነታቸው ባልታወቁ አፋኞች በሐይል ተወስዶ ደብዛው መጥፋቱ ሲነገርለት የቆየው ወጣቱ እንጅነር እምብዛ ታደሰ ፤ በጨካኝ የከተማ ሽብር ተልእኮዎች አስፈፃሚ ወንጀለኞች ተገድሎ ፤ በፌደራል ፖሊስ የፀጥታ ሐይሎች በተከናወነ አሰሳ ፣ በትላንትናው እለት ከረፋዱ አምስት ሰዓት በዓይደር ልዩ ስሙ ማረምያ ቤት በተባለ ስፍራ ተገድሎ ብቻ ሳይሆን ለጅቦች ከተጣለበት ስፍራ ቁርጥራጭ የሰውነት አካላቱን በመለየት በተጨማሪ ምርመራም፤ በአረመኒያዊ አፈፃፀም በጭካኔ መገደሉን ለማረጋገጥ ተችሏል።
ይህ በእጅጉ ከሰብአዊ ፍጡር የማይጠበቅና የሚኮነን አረመኔያዊ የግድያ ወንጀል እየተፈፀመ ያለው፤ በተለይ ትግራይ በአሁኑ ግዜ ላጋጠማት ችግር የመፍትሔ አካል በመሆን ከግዚያዊ አስተዳደሩ ወቅታዊ የተልእኮ አቅጣጫ በመውሰድ ወገኖቻችን ለተጨማሪ ሞትና ስቃይ ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በዘመቻ መልክ በቅንጅት በመተግበር ፣ የምግብ እና የህክምና እርዳታዎችን ተደራሽ ማድረግ፣ የያዝነው ክረምት የዝናብ ፀጋ ገበሬያችን እንዳያልፈው እርሻ ስራን ለማስጀመር ርብርብ በሚደረግበት ወቅት፣ መሰረተ-ልማቶች ወደ ስራ ለማስገባት ሌት ተቀን በሚለፉ፣ ፋብሪካዎችን ወደስራ በመመለስ የስራ ዕድል ፈጠራው ዳግም ለማንሰራራት በሚባክኑ፣ ጨለማን ገፈው ብርሃን ለህዝባቸው ለማቅረብ በሚዳክሩ፣ የጤና ተደራሽነት እንዲሻሻል በሚመክሩ፣ የትግራይ ህዝብ ሃብት የሆኑትን የትእምት ፋብሪካዎች የምር የህዝብ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ሚገኙ ወጣቶች ወዘተ፣ በግጭቶች መስፋትና መካረር በዘላቂነት በትግራይ ውስጥ ሊፈጥር የሚችለው ተጨማሪ ቀውስ እንዳይባባስ ትንቅንቅ በያዝንበት በዚህ ወቅት ነው። ይህም የትግራይን እምባ የማበስ መስዋእት የሚያስከፍል የሰማእት ወጣቶች ተልእኮ ለአረመኔዎች ደንታ የማይሰጥበት የጭካኔ ጠርዝ መኖሩን እያስቃኘን ይገኛል።
በመሆኑም እስካሁን ይህን በጎና ቀና ተግባር በመከወን ህዝባቸውን እየረዱ የነበሩ እስካሁን ድረስ በተጠናቀረ መረጃ በአሁኑና መሰል እኩይ ወንጀሎች በትግራይ ከሐምሳ በላይ ወጣት የህይወት አድን እና የማህበረሰብ አገልግሎት ሰጪ ንፁሐን፤ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ወይም ወታደራዊ ተሳትፎ ፍፁም ገለልተኛ የሆኑ አገልጋዮችን ህይወት በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ቦታዎች በከንቱ የመቀጠፋቸው አሳዛኝ ዜና መላው ማህበረሰባችን ነቅቶ ሊከታተለው የሚገባ ጉዳይ ሆነዋል።
ገዳዮች ይህንን መሰል ወንጀላቸውን ከመፈፀማቸው በፊትና በኃላ ያለ ህፍረትና መሸማቀቅ በሞትና መከራ ወኪል ልሳኖቻቸው በግልፅ በድፍረት የሚናገሩ ከመሆናቸውም በላይ፤ በሐሳብና ተግባራቸውም በትግራይ ወጣቶች ሞትና መከራ የመነገድና የመደመጥም ተልእኮ እንዳላቸውም አጥፊው ቡድን እና ደጋፊዎቹ ሃላፊነት ወስደው በአደባባይ ሽንጣቸውን ገትረው መስክረዋል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ በየትኛውም የተግባርም ሆነ በህግ የተቀመጠ የተልእኮ ወሰን መለኪያዎች በተለይ ባለፋት ጥቂት ሳምንታት የተሻሻሉ የአደጋ ጊዜ አመራር መርህዎችን በተከተሉና ሀላፊነት እና ወገናዊነት በሚሰማቸው የህዝብ ልጆች ፣ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትና የተቋረጡ አስፈላጊ ማህበራዊ አገልግሎቶችን የማስቀጠል ፣ነፍስ አድን ስራዎችን ተደራሽ ለማድረግና ለህዝቡ ጊዜያዊ እፎይታ ለመስጠት በሚያስችሉ የዘመቻ ስራዎች ተሳትፎ፣ አንፃራዊ የህብረተሰብ ተሳትፎ መሻሻል ባገኘበት በአሁኑ ጊዜ መፈፀሙ ፣ የጥፋት ሀይሎቹ እኩይ አላማቸውን ከህብረተሰቡ የህልውና ጉዳይ በላይ ያስቀደሙ መሆናቸውን በግልፅ የሚያሳይ፤ ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ እነዚህን የመከራ ነጋዴዎች በቃ ሊላቸው የሚገባበት የመጨረሻው ደቂቃ ላይ እንደምንገኝ በጥብቅ የሚያመላክት ሀቅ ነው።
የጊዚያዊ አስተዳደሩ ይህ በተለይ በትግራይ ወጣቶች ላይ የተቃጣ እና ወጣቶች በክልላቸውና በአገራቸው ጉዳይ ላይ በአዎንታዊ አግባብ የሚያደርጉትን የነቃ ተሳትፎና አበረታች ጅማሬ ለማሸማቀቅ የተዘረጉ የጥፋት በትሮችን ከሚመለከታቸው የፀጥታና የደህንነት አካላት ጋር በተቀናጀ እርምጃ ለማክሸፍ የሚሰራም መሆኑን ሁሉም ሊገነዘቡት የሚገባ ጉዳይ ነው ።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተጣለበትን ተልእኮ በራሱ ጀምሮ በራሱ ለመጨረስ የማይኮፈስና በትግራይ ተጨማሪ ሞትና ሰቆቃ እንዳይበዛ የማድረግ የሐላፊነት እድልን በስስታምና አግላይ አመለካከት ማስፈፀም ተገቢ አይደለም በሚል ቅን እሳቤ የአሳታፊነት እድሎችን ለማስፋት የተጠኑ እርምጃዎችን ቢያደርግም፣ አንዳንድ ክፋዎች ይህንን አሳታፊነት እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ከውስጣችን ሆነው ቅን አገልግሎት የሚሰጡ እንጅነር እምብዛ የመሳሰሉ ለህዝብ የተሰጡ ወጣቶችን ህይወት እስከመቅጠፍ የደረሰ ነውረኛ ሴራ ውስጥ በተግባርና በሐሳብ ጭምር ተካፋይ መሆናቸውን የሚያመላክቱ ተጨባጭ ማስረጃዎች ተገኝተዋል። በተገቢና ጠንካራ ምርመራ ሒደት ውስጥ በማሳለፍም አስፈላጊውን አፋጣኝ ፣ የማያዳግምና አስተማሪ የሆነ የማስተካከያ እርምጃዎችንም እንደሚወስድ ከወዲሁ በፅኑ ያስታውቃል።
በዚህ አጋጣሚ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር በእንጅነር እምብዛ እና በአጠቃላይ ባለፋት ተከታታይ ወራት በንፁሐን አገልግሎት ሰጪ ሰራተኞች ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ጥቃቶች በጥብቅ እየኮነነና እያወገዘ ፤ ለሟች እንጅነር አርቲስት እምብዛ ታደሰ እና ሌሎች በለጋ እድሜያቸው የተቀጠፉ የጊዜያዊ አስተዳደር አባላት ቤተሰቦች ፣ የስራ ባልደረቦችና አፍቃሪዎቹ በሙሉ ፈጣሪ መፅናናት እንዲሰጥልን እየተመኝን ፣ በወንድማችን እንጅነር እምብዛ ታደሰ አሰቃቂ ህልፈት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልፃለን።