በሆሩ ጉዱሩ ወለጋ ዞን 433 የአሸባሪው ሸኔ አባላት ሲደመሰሱ 115ቱ መማረካቸው ተገለፀ

የአሸባሪው ሸኔ አባላት

ጥር 3/2014 (ዋልታ) በሆሩ ጉዱሩ ወለጋ ዞን እስካሁን በተካሄደ ኦፕሬሽን 433 የአሸባሪው ሸኔ ቡድን አባላት ሲደመሰሱ 115 አባላቱ ደግሞ መማረካቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

የዞኑን ሰላም ወደ ቦታው ለመመለስ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በቅንጅት በመስራት አስተማማኝና ውጤታማ ኦፕሬሽን በዞኑ እየተካሄደ ስለመሆኑ የገለፁት የሆሩ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ በቀለ ደቻሳ ናቸው።

በዚህም ወደ 433 የአሸባሪው ሸኔ ቡድን አባላት ሲደመሰሱ 115ቱ ተማርከዋል፤ የቡድኑ የመረጃ እና የሎጅስቲክስ ክንፍ የሆኑ ወደ 623 የሚደርሱ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉንም ተናግረዋል።

እንዲሁም ጠላት ሲጠቀምባቸው የነበሩ ዘመናዊና ኋላ ቀር የጦር መሳሪያዎችም ገቢ የተደረጉ ሲሆን የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ በማጤን አስፈላጊውን ምላሽ እየሰጠን ነው ብለዋል።

ሕዝቡን በማሳተፍና በማደራጀት ሰላምን የማረጋገጥ ስራ በጋራ እየተሰራ ነው ያሉት አስተዳዳሪው በቀለ ደቻሳ አመራሩም አሸባሪውን ቡድን ከዞኑ ለማጥፋት በእቅድ እየተመራ አመርቂ ሚና እየተጫወተ ነው ሲሉም አክለዋል።

አሁን ላይ ቡድኑ በዞኑ የሚያካሂደው መስፋፋት ሙሉ በሙሉ እየደረቀ ሲሆን በአጭር ጊዜም ዞናችንን ከአሸባሪው ሸኔ ነፃ በማድረግ ለሕዝባችን የተሟላ ሰላም እናረጋግጣለን ነው ያሉት።

በደረሰ አማረ (ከሻምቡ)