መጋቢት 08/2013 (ዋልታ) – በሎስ አንጀለስ እና አካባቢው ነዋሪ የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያዊ እና ኤርትራዊ አሜሪካውያን የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ በመደገፍ እና የተለያዩ የአሜሪካ መንግስት አካላት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና በመቃወም የኮንግረስ አባል ካረን ባስ የሎስ አንጀለስ ጽ/ቤት ፊት ለፊት ሰልፍ አካሂደዋል።
የአሜሪካ ኮንግረስ የካሊፎርኒያ ተመራጭ የሆኑትና በኮንግረሱ የአፍሪካ፣ የዓለም ጤና፤ የሰብዓዊ መብቶች እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን የሚከታተለው ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ካረን ባስ በቅርቡ በኮንግረስ ያቀረቡት ኢትዮጵያን የተመለከተ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ሚዛናዊነት የጎደለው እና በተጨባጭ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ መሆኑን በመጥቀስ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡ ውድቅ እንዲደረግ እና የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ በሚያንፀባርቅ መልኩ እንዲዘጋጅ በመጠየቅ ያወጡትን መግለጫ ቅጂ ለጽ/ቤቱ አስገብተዋል።
ሰልፈኞቹ ኢትዮጵያን በተመለከተ በተለያዩ የዩናይትድ ስቴትስ የመንግስት አካላት እየወጡ ያሉ የተዛቡ መረጃዎችን የሚቃወሙ፣ የአሜሪካ መንግስት ትክክለኛ መረጃ ላይ የተሰረተ ውሳኔ እንዲሰጥ የሚጠይቁ እና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚታየውን ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዙ መፈክሮችን ማሰማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።