የህዳሴ ግድብ እንዲጠናቀቅ ሕዝቡ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ

መጋቢት 08/2013 (ዋልታ) – ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንዲጠናቀቅ ህዝቡ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ገለፁ።

ዶክተር አረጋዊ በርሄ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቅት፣ የህዳሴው ግድብ የአገሪቱ ተስፋ መሆኑን ከህፃን እስከ አዋቂ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ስላመነበት አሁን ላይ ሥራው እንዲጠናቀቅ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።

ሕዝቡ በጉልበቱ፣ በእውቀቱ እና ባለው ሁሉ የግድቡን ሥራ እያገዘ እንደሆነ ያመለከቱት ዶክተር አረጋዊ፣ በመንግሥት በኩል የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችንም በትኩረት እየተከታተለ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በነበሩባት የውስጥ የቤት ሥራዎቿ ምክንያት እስከ ዛሬ ድረስ በገዛ ውሃዋ ሳትጠቀም ቆይታለች ያሉት ዶክተር አረጋዊ፣ አሁን ደግሞ ጊዜው ደርሶ አልምታ ለመጠቀም እየሠራች ነው ብለዋል። በዚህ ሀብቷ አትጠቀሚ ማለት ከፍተኛ ስህተት ከመሆኑም በላይ የቀኝ ግዛት ሥነ ልቦና የፈጠረው ችግር መሆኑን አመልክተዋል።

ሱዳንና ግብጽ አሁን እያነሱ ያለው አጀንዳ መሰረታዊ አይደለም የሚሉት ዶክተር አረጋዊ፣ ምክንያቱም ለብዙ ዘመናት ውሃውን ብቻ ሳይሆን አፈራችንንም በአግባቡ ተጠቅመውበታል፤ አሁን ደግሞ ጊዜው በጋራ የመልማት ነው ብለዋል።