በመዲናዋ የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ በቅንጅት እየተሰራ ነው – የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ


መስከረም 5/2016 (አዲስ ዋልታ) በመዲናዋ የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።

በአዲስ አበባ ከተማ የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር ተከብረው እንዲውሉ ከአራዳ ክፍለ ከተማ የሰላም ሠራዊት አባላትና ከፀጥታ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሚደቅሳ ከበደ የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበሩ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ቢሮው በከተማዋ ካሉ የሰላም ሠራዊት አባላትና ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸው የመዲናዋ ነዋሪዎችም የሰላም ሠራዊቱን እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአደባባይ በዓላት በሰላም እንዲከበሩና ኅብረተሰቡ ከሠላም ሠራዊትና ከጸጥታ አካላት ጋር በቅርበት የሚሰራውን ሥራ እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዲ ሙሉነህ በበኩላቸው ሰላም በመዲናዋ እንዲረጋገጥ የሰላም ሠራዊቱ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ ነው ብለዋል።

የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ኃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶቻቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲከበሩ የሰላም ሠራዊት አባላት ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎ በአራዳ ክፍለ ከተማ እነዚህን የአደባባይ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ከሰባት ሺህ በላይ የሰላም ሠራዊት አባላት ተደራጅተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ኃላፊው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ የሰላም ሠራዊት አባላትም የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላትን ሊያውኩ የሚችሉ ተግባራትን በመከላከል በሰላም እንዲከበር በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።