በምርጫ ወቅት ከስሜታዊ ንግግሮችና ድርጊቶች መቆጠብ ይገባል – ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ

መጋቢት18/2013(ዋልታ) – ምርጫው ሰላማዊና ፍትሐዊ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ በህዝቦች መካከል መቃቃርን ከሚያስከትሉ ስሜታዊ ንግግሮችና ድርጊቶች ሊቆጠብ እንደሚገባ ሊቀጳጳስ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ አስታወቁ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ ወ ቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ እንዲሁም የድሬዳዋና የጅቡቲ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ በምርጫ ጉዳይ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ምርጫው ሰላማዊና ፍትሐዊ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ በህዝቦች መካከል መቃቃርን ከሚያስከትሉ ስሜታዊ ንግግሮችና ድርጊቶች በመቆጠብ፣ አገርን አንድ ዕርምጃ ወደፊት ለሚያራምድ የፖሊሲ አማራጭ መመርመርና መከተል አለባቸው፡፡

ለፓርቲዎች ድል የሚሰጥ እግዚአብሔር ቢሆንም ምዕመናኑ ግን ምርጫው ፍትሐዊና ሰላማዊ እንዲሆን ለሰላም ዘብ መቆም ሃይማኖታዊ ግዴታቸው ከመሆኑም በተጨማሪ አገራዊ ግዴታቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ተፎካካሪ የፖሊቲካ ፓርቲዎች እግዚአብሔር የሚጠየፋቸውን ያልተገቡ ቃላት፣ የአገራችንን ቁስል የሚያባብስና ህዝቡን የሚያራርቅ ተግባራትን በቅስቀሳ ወቅት እንዳይጠቀሙ አደራ ብለዋል፡፡ ህዝቡ በተለይ ወጣቱ ክፍል ዛሬ የሚፈጠረው ችግር ነገ የእሱ ዕዳ መሆኑን በመገንዘብ፣ ፓርቲዎቹ የሚያቀርቡት አማራጭ ፖሊሲዎችን ከስሜት ይልቅ በስሌት እንዲያጤንም አሳስበዋል፡፡