‹‹በምዕራብ ትግራይ በኩል መተላለፊያ ኮሪደር ይከፈት የሚለው ግፊት ተቀባይነት የለውም›› – አቶ ምትኩ ካሳ

ሐምሌ 27/2013 (ዋልታ) – በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ለሚሹ ተረጂዎች እርዳታ ለማቅረብ በሚል አንዳንድ ምዕራባዊያንና ተቋሞቻቸው በምዕራብ ትግራይ በኩል መተላለፊያ ኮሪደር ይከፈት የሚለው ግፊታቸው ተቀባይነት እንደሌለው የብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ አስታወቁ ።
እርዳታ አቅርቦቶች በፌዴራል መንግስትና በአፋር ክልል ከፍተኛ ጥረት ለትግራይ ህዝብ እየደረሰ መሆኑን ገለጹ።
አቶ ምትኩ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ መንግስት ያሳለፈውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ባለመቀበል በአማራ እና በአፋር ክልሎች ላይ ትንኮሳ እየፈጸመ ያለው አሸባሪው ህወሓት ለትግራይ ክልል ተረጂዎች የሚቀርብን እርዳታ የያዙ ከ170 በላይ ተሽከርካሪዎችን አግቶ በማቆየቱ በክልሉ ያሉ ተረጂዎች ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጠዋል።
ይህንን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራትና ተቋሞቻቸው ከሱዳን ቀጥታ እርዳታ ለማስገባት በሚል በምዕራብ ትግራይ በኩል መተላለፊያ ኮሪደር ይከፈት የሚል ጥያቄዎችን ማቅረባቸውን ጠቁመዋል።
አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራትና ተቋሞቻቸው ይህንን ይበሉ እንጂ መንግስት ለተረጂዎቹ እርዳታ ለማቅረብ የጅቡቲው መስመር በቂ መሆኑን በማሳወቅ ተጨማሪ ኮሪደር እንደማይከፈት ማሳወቁን በዚህም የጸና አቋም እንዳለው ለኢፕድ አስታውቀዋል።