ሐምሌ 26/2013 (ዋልታ) – የሀገር አንድነትን አደጋ ላይ ለመጣል የሚሰራው ህገ-ወጥ ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ ለመዝመት የቆረጡ አራት የገቢዎች ሚኒስቴር ሰራተኞች ሽኝት ተደርጎላቸዋል፡፡
በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ “ሀገር እንዳትፈርስ ውድ ህይወታችሁን ለመስጠት ስለወሰናችሁ እናመሰግናለን” ብለዋል የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው፡፡
አማፂው የህወሓት ጁንታ ቡድን ”እኔ የማልዘውራት ሀገር ትፍረስ” በሚል የማይሳካ ህልም እንዲመክን መላው ኢትዮጵያውያን የጀመሩትን ትግል ለመቀላቀል የወሰኑ ሰራተኞቻችን ትልቅ ክብር አለንም ነው ያሉት፡፡
የሚጠበቅብንን ሀገራዊ ሀላፊነት ተወጥተን ገቢ በአግባቡ መሰብsብ ማለት ጁንታውን እንደመደምሰስ ይቆጠራልም ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
በቀጣይም ሰራዊቱን በገንዘብ እና በቁሳቁስ ለመደገፍ የተጠናከረ ስራ እንደሚጠበቅ ገልፀው፣ ለዚህም መላው ሰራተኛ ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
በሽኝት መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት ዘማች ሰራተኞች በበኩላቸው የተጋረጠብንን ሀገራዊ አደጋ ለመመከት ሁሉም በአቅሙ መደገፍ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡
መላው የገቢዎች ሰራተኞችና እና አመራሮች የተጣለባቸውን ሀላፊነት ከየትኛውም ጊዜ በላይ እንዲወጡና ግንባር ላለው ሰራዊት ደጀን እንዲሆኑም ጠይቀዋል፡፡
ከዘማቾቹ መካከል ሁለቱ በምስራቅ አዲስ አበባ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እና ሁለቱ ደግሞ በኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስር የሚገኙ መሆናቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡