በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት ያሉ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ውይይት ተደረገ

ሰኔ 08/2013 (ዋልታ) – በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሌንጮ ባቲ በሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አህመድ ቀጣንና በሳኡዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከቆንስላ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተሚም አል ዶሰሪ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ በሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና በሌሎች የጋራ ቀጣናዊ ጉዳዮች እንዲሁም ሳኡዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ዙሪያ መምከራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከዚህም ጋር በተያያዘ በእስር ቤት ያሉ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ጉዳይ፣ የመኖሪያ ፈቃድ የተቃጠለባቸው እና በተለያዩ ምክንያቶች ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሳኡዲ አረቢያ ሲኖሩ የቆዩ ዜጎች በፈቃዳቸው ያለምንም ገንዘብ መቀጮና እስራት በፍላጎታቸው ወደ አገር በሚመለሱበት አግባብ፣ ሰሞኑን እየተደረገ ባለው የፖሊስ አፈሳ እንዲሁም የዜጎች የሰብዓዊ መብት አያይዝ ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል።