በሲዳማ 3ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ተጀመረ

ሰኔ 08/2013 (ዋልታ) – በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት 3ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ማስጀመሪያ ስነሥርዓት በሸበዲኖ ወረዳ ተካሂዷል።

የሲዳማ ክልል ፕሬዝዳንት ደስታ ሌዳሞ በአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርኃግብር የሲዳማ ህዝብ በላፉት ሁለት አመታት የፖለቲካ ጥያቄውን እየጠየቀ ሀገራዊ ኃላፊነቱንም ጎን ለጎን ሲወጣ እንደነበር ገልጸው፣ ዘንድሮ የሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ህዝቡን የህይወት ዋጋ ሲያስከፍል የነበረ ጥያቄ በተፈታ ማግስት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

በመርኃግብሩ ላይ የተገኙት የኢፌዲሪ ግብርና ሚኒስትር ኡመር ሁሴን በበኩላቸው፣ ክልሉ “ኢትዮጵያን እናልብስ” የተሰኘውን ንቅናቄ ተቀብሎ እየሰራ ያለውን ስራ በማድነቅ ለጎረቤት ሀገራት የሚሰጠው ከአንድ ቢሊየን ችግኝ ውስጥ ክልሉ እስካሁን 5 ሚሊየን ችግኞች ማዘጋጀት መቻሉን አድንቀዋል፡፡

የእለቱ የክብር እንግዳ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የሁለቱ ክልል ህዝብ አብሮ የመቆም ታሪክ አጠናክረን አብሮ እንዲለማ እንሰራለን ብለዋል፡፡

አክለውም ለፖለቲካዊ መፍትሔ አባቶቻችን አብሮ እንደቆሙ አሁን ያለው ትውልድም ለኢኮኖሚያዊ መብት በጋራ በመቆም ታሪካዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የሲዳማ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ መስፍን ቀሬ በክልሉ በዚህ አመት 300 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እስካሁን 270 ሚሊየን ችግኞችን ማዘጋጀት መቻሉን ገልጸዋል።

ላለፉት አመታት በአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ፕሮግራም የተሰራው ስራ ከ85 በመቶ በላይ ስኬታማ እንደነበርም ተናግረዋል።

በመርኃግብሩ ላይ የፌዴራል እና የተለያዩ የክልል መንግስታት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

(በሶሬቻ ቀበኔቻ)