በስንዴ ምርት የተገኘው ውጤት ለሌሎች ስራዎች ስንቅ ነው – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

ሚያዝያ 29/2015 (ዋልታ) በስንዴ ምርት የተገኘው ውጤት ለሌሎች ስራዎች ስንቅ ስለመሆኑ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ተናገሩ።

በሳይንስ ሙዚየም ከተከፈታው የግብርና እና ሳይንስ ዐውደ ርዕይ ባሻገር የፓናል ውይይት እየተካሄደ ሲሆን በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የግብርና ሚኒስትሩ የግብርናው ዘርፍ ከነዋሪዎች ጋር የተቆራኘ ከመሆኑ ባሻገር በአጠቃላይ ምጣኔሀብታዊ እድገት ላይ አበርክቶ እያደረገ ያለ ዘርፍ ነው ብለዋል።

ነገር ግን ዘርፉ በቴክኖሎጂና በኢንቨስትመንት ባለመታገዙ ባህላዊ ሂደቶችን ይዞ እንዲቀጥል ሆኖ በመቆየቱ እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናችን እንዳናረጋግጥ አድርጎን ቆይቷል ነው ያሉት።

ሆኖም ባለፉት ዓመታት መንግስት ዘርፉን ለማዘመን ልዩ ትኩረት በመስጠቱ በዘርፉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተዋል።

ባለፈው ዓመት ብቻ አርሶ አደሩ የግብርና ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ 36 ቢሊየን ብር ድጎማ መደረጉን የገለጹት ሚኒሰትሩ አርሶ አደሩ ብድር እንዲያገኝ የማመቻቸት ስራ በስፋት መከናወኑንም ጠቁመዋል።

ዝናብ ከመጠበቅ ይልቅ በበጋ መስኖ ልማት የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን አንስተው ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ወደ ውጭ ስንዴ መላክ መጀመሯ ከስኬቶቹ መካከል እንዱ ነው ብለዋል።

በስንዴ የተገኘው ውጤት ለሌሎች ስራዎች ስንቅ እንደሚሆንም በማንሳት በስንዴ የተገኘውን ስኬት በሌሎች ሰብሎች መድገም ይገባል ሲሉም አክለዋል።

በትዕግስት ዘላለም